መዲናዋን በየዘመናቱ የመሩ ከንቲባዎች ያሳረፏቸው አሻራዎች አገር በቅብብሎሽ እንደሚገነባ ማሳያዎች ናቸው

18

ጥር 16/2014/ኢዜአ/ አዲስ አበባን በተለያየ ዘመን የመሯት ከንቲባዎች ያሳረፏቸው አሻራዎች አገር በትውልድ ቅብብሎሽ እንደሚገነባ ማሳያ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከ57 ዓመት በኋላ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በሚልቅ ወጪ እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ትናንት ተመርቋል።

የከተማዋ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ሃላፊ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ እድሳቱ ሕንጻው ለቀጣይ በርካታ ዓመታት እንዲቀጥል ታሳቢ ተደርጎ መከናወኑን ገልጸዋል።

በውስጡ በርካታ ሰዎችን የሚያስተናግዱ ቢሮዎች፣ የመኪና ማቆሚያና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ተካተውበት መታደሱንም ተናግረዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያደስነው ሕንጻውን ብቻ ሳይሆን በቢሮክራሲ የተተበተበውን የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ለሕዝባችን ያለንን ፍቅርና አክብሮትም ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ያደስነው ሕንጻ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ቅርስና ሃብት ነው ያሉት ከንቲባዋ ማዘጋጃ ቤቱ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ መታደሱን ገልጸዋል።

'አዲስ አበባን በተለያየ ዘመን የመሯት ከንቲባዎች ያሳረፏቸው አሻራዎች አገር በትውልድ ቅብብሎሽ እንደሚገነባ ማሳያዎች ናቸው' ብለዋል።

የማዘጋጃ ቤት ሕንጻ የኋላ ጠንካራ ታሪካችንን የምናወሳበት፣ የመጪውን ትውልድ ብሩህ ተስፋ የምናሳይበት ነው ብለዋል።

ከግንቦት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከናወነው የሕንጻው እድሳት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትም ጠቅሰዋል።

የማዘጋጃ ቤቱ ሕንጻ ቀደም ሲል ለምረቃ ከበቁት የመስቀል አደባባይና አብርሆት ቤተ መጻሐፍት ቀጥሎ የከተማዋ ሶስተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም