በኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ በአገር ልማት የድርሻችንን እንወጣለን- ዳያስፖራዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ በአገር ልማት የድርሻችንን እንወጣለን- ዳያስፖራዎች

ዲላ ጥር 15/2014--(ኢዜአ) በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ በአገር ልማት የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ዳያስፖራዎች አስታወቁ።
የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ሀገራዊ ጥሪን ተከትለው ወደ ሀገር ቤት ለመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የዞኑ ተወላጆች ጋር በዲላ ከተማ የምክክርና የጉብኝት መርሀግብር አካሂዷል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የውይይቱ ተሳታፊ ዳያስፖራዎች መካከል ዶክተር ብርሃኑ በለጠ ከ26 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገራቸው መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ያልተገባ ጫና በመገንዘባቸው ባሉበት አገር በ"በቃ" ንቅናቄ ሲሳተፉ እንደነበረና አሁንም ለአገራቸውና ለትውልድ ለመስራት መነሳሳታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም በዞኑ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ከመሳተፍ ባለፈ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በማካፈል በአገር ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ያደረጉትን ጥሪ ተቀብለው ከቻይና ወደ አገር ቤት እንደመጡ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ቅድስት ፋንታሁን ናቸው።

ጥሪውን ተቀብሎ መምጣት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፣ በፍራፍሬ ልማትና ማቀነባበር ዘርፍ ለመሰማራት ለዞኑ አስተዳደር የመነሻ ሃሳብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
"አገራችን ከገባችበት ውስብስብ ችግር እንድትወጣ ከማገዝ ጎንለጎን ድህነትን በዘላቂነት ለማሸነፍ በሰው አገር ያፈራናትን ቅሪት፣ እውቅትና ልምድ ወደ አገራችን ማምጣት አለብን" ብለዋል።
አገር ቤት ሲገቡ የተደረገላቸው አቀባበልና የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ከጠበቁት በላይ እንደሆነባቸው የገለጹት ደግሞ ከአሜሪካ ቺጋጎ የመጡት አቶ አብደላ አበራ ናቸው።
በኢትዮጵያ ሰላም እንደሌለ በውጭ መገናኛ ብዙሀን ሲተላለፍ የነበረው ዘገባ እጅግ የተሳሳተና ሀሰት እንደነበር በሀገር ቤት ቆይታቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
"የኢትዮጵያን ሰላም በማሳየት የሀሰት ፕሮፓጋንዳውን እናጋልጣለን፤ በሀገራችን ልማት ላይ በንቃት በመሳተፍ የኢኮኖሚ ጫናውን ለማርገብ የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል።
ዳያስፖራው በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሳተፍ በአገሩ ልማት ግንባር ቀደም እንዲሆን ሁኔታዎች እንደተመቻቹ የገለጹት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አክሊሉ በደቻ ናቸው ።
በተለይ በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ዳያስፖራዎች ከ50 ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በዲላና በይርጋጨፌ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁና መሰረተ ልማት የተሟላላቸው መካከለኛ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለሃብቶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው "የመከፋፈልና የመገፋፋት ጊዜ አልፎ ዛሬ ስለአካባቢያችንና ስለ ሀገራችን ልማት በጋራ መምከራችን በቀጣይ ብሩህ ጊዜ እንደሚጠብቅን ያሳያል" ብለዋል።
ዳያስፖራዎች በእናት አገራቸው ላይ የሚደረገውን ጫና ለመከላከል ያሳዩትን ተጋድሎ በልማት በመድገም ሀገራቸውን ከኋላ ቀርነትና ከድህነት ለማላቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በዞኑ በኢንቨስትመንትና በተለያዩ መስኮች መሳተፍ ለሚፈልጉ ዲያስፖራዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዞኑ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጥዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ በዞኑ ስለሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለዳያስፖራዎች ገለጻ ተደርጓል።