ዳያስፖራዎች በሲዳማ ክልል የልማት ስራዎችን ጎበኙ

108

ሀዋሳ፣ ጥር 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለዳያስፖራው የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዳያስፖራዎች በሲዳማ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ተሰርተው የተጠናቀቁና በሥራ ላይ ያሉ የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።

ከአሜሪካ የመጡት አቶ መንግስቱ ገዳና በሰጡት አስተያየት፤ ከኢትዮጵያ ርቀን በነበርንበት ወቅት ሀገር ውስጥ ሠላም እንደሌለና ምንም ዓይነት የልማት ሥራ እየተከናወነ አለመሆኑን ስንሰማ ነበር ብለዋል፡፡

ወደ ሀገሬ መጥቼ ባየሁት ነገር እጅግ ኮርቻለው ያሉት አቶ መንግስቱ፤ የሲዳማ ክልል አስተዳደሩ እየሰራ ያለውን ልማት አድንቀዋል።

ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ያሉ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ የክልሉ መንግስትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ላታሞ፤ ክልሉ የህዝቡን የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመልስ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በመንግስት በተመደበ 506 ሚሊዮን ብር  ከ1 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር በላይ አዲስና ነባር የጠጠር መንገድ ጥገና ስራዎች መከናወናቸውን ጠቀሰው፤ በምህንድስናና መሰል መስኮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ከ430 በላይ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሳተፉ በማድረግ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አስረድተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በተገኙበት በተካሄደው ጉብኝት ቦሪቻ፣ ደራራ፣ ሎካ አባያ፣ አለታ ጩኮ፣ አለታ ወንዶ፣ ቦና እና ቡርሳ ወረዳዎች ላይ የተጠናቀቁና በሥራ ላይ ያሉ የመንገድ ልማት ፕሮጀክቶች ተቃኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም