የወጣቶች ሊግ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚውል የግንባታ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

73

አዲስ አበባ ፣  ጥር 14/2014(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የግንባታ ቁሳቁስ ድጋፍ አበረከተ።

ሊጉ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመገኘት ያበረከተው ድጋፍ ለቤት መስሪያ የሚያገለግል ቆርቆሮ እና ምስማር ነው።

የሊጉ ፕሬዚዳንት ወጣት መለሰ አባተ ሊጉ ቀደም ሲልም በክልሎቹ ለሚገኙ ተጎጂዎችና ለመከላከያ ሠራዊት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

"ወጣትነቴ ለሀገሬ" በሚል እስካሁን 10 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ መደረጉንና የዛሬው የግንባታ ቁሳቁስም በዚሁ ውስጥ የተካተተ መሆኑን ተናግሯል።

ድጋፉን የተረከቡት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ"ወጣትነት ለሀገሬ" ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኤርሚያስ ማቲዮስ የተሰባሰበውን የአይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ በቅርቡ ወደ አካባቢዎቹ በመሄድ እንደሚያስረክቡ ገልጸዋል።

በአማራና በአፋር ክልሎች ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት መሳተፍ የሚሹ አካላት ለሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ድጋፋቸውን ማቅረብ እንደሚችሉም አስታውቀዋል።

ከአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበርም 110 ሺህ ብር የሚያወጣ የቆርቆሮ ድጋፍ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም