በክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሰማራት የሚፈልጉ ዳያስፖራዎችን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል

አሶሳ፤ ጥር 14 / 2014 (ኢዜአ) በኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መሰማራት የሚፈልጉ ዳያስፖራዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ለማስተናገድ መዘጋጀቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ጽንሰ እና ደለል ወርቅ፣ እምነበረድ፣ አባይን ጨምሮ ትላልቅ ወንዞች፣ ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚውል ሰፊ ለም መሬት፣ የቆላ ቀርከሃ፣ እጣን እና የድንጋይ ከሰል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ክልሉ የተፈጥሮ ሃብቱን በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ለሃገር ልማት እንዲውል በትኩረት እየሠራ ነው፡፡

ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብቱን ማስተዋወቅ ጨምሮ በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶች ላይ የውይይት መድረክ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ለኢንቨስትመንት ማነቆዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በዝርዝር እንደሚያቀርቡ ገልጸው፤ በተጨማሪ የክልሉ ኢንቨስትመንት ሃብት ላይ ተጨማሪ ዝርዝር ጥናት እንደሚካሄድ ነው ያመለከቱት፡፡

በተለይም በቅርቡ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ዳያስፖራዎች ወደ ክልሉ ቢመጡ ቢሮው የኢንቨስትመንት ፈቃድን ጨምሮ የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት  ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አቶ አመንቴ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት ለሃገር በሚጠቅም መልኩ በማልማት ተስፋ ሰንቀን እየሠራን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዳያስፖራው በአካል ተገኝቶ ክልሉን በመጎብኘት ችግሮቹን ተጋርቶ የመፍትሄው አካል ጭምር በመሆን የክልሉ የተፈጥሮ ሃብት እንዲለማ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሠማሩ ባለሃብቶች ማህበር ሰብሳቢ አቶ አብዱልማሙድ ኢብራሂም፤ የመንግስትን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሃገር ቤት ለመጡ ኢትዮጵያውያን ታላቅ አክብሮት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡

ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያን በርካታ የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም በድህነት ውስጥ የሚገኙ ዘጎችን ከድህነት ለማውጣት እውቀታቸውን እና ሃብታቸውን አሰባስበው እንደሚሠሩ ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡

በክልሉ በተሰማሩባቸው የግብርና ኢንቨስትመት ዘርፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚመሩ መንግስታዊ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱን ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በክልሉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመውሰድ ረጅም ጊዜ ይፈጅ የነበረው ችግር በአሁኑ ወቅት መፈታቱን ጠቅሰዋል፡፡

ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ደሳለኝ ፈንታው በሰጡት አስተያየት፤ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በ “በቃ” እንቅስቃሴ ለሃገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ የሚያናፍሱት የተሳሳተ መረጃ ሳይበግራቸው የመጡ ዲያስፖራዎች  በክልሉ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ማድረግ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የነዋሪውም ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ መገኛ መሆኑን ያወሱት ነዋሪው፤ በተለይም በክልሉ የተሻለ ሠላም ባለበት አሶሳ ዞን ያለውን የወርቅ ሃብት ጠቅሰዋል፡፡

ሃብቱን ለዳያስፖራው በማስተዋወቅ  መስራት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቱሪዝም፣ ዓሳ ልማትና ትራንስፖርትን ጨምሮ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንደሚፈጠር ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም