በድሬዳዋ ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለዕድለኞች ሊተላለፉ ነው

40

ድሬዳዋ ፤ ጥር 14/2014 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሚቀጥሉት ሁለት ሣምንታት ለዕድለኞች በዕጣ እንደሚተላለፉ የአስተዳደሩ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ።

በአስተዳደሩ በተጨማሪ 524 መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዓሊ መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተገነቡ 358 የጋራ መኖሪያ ቤቶች  እስከተያዘው ወር መጨረሻ ለነዋሪዎች በዕጣ ይተላለፋሉ፡፡

በዕጣ ለነዋሪዎች የሚተላለፉት ቤቶች ባለ 10/90 እና ባለ 20/80 ናቸው፡፡

እነዚህ ባለአራት ወለል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከስቱዲዮ እስከ ሦስት መኝታ ክፍሎች እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ቤቶቹ የሚተላለፉት ተገቢውን መስፈርት አሟልተው ለተገኙ ለ5 ሺህ 300 ነዋሪዎች ይሆናል ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለማቃለል በማህበር ለተደራጁ መምህራን ቦታ በማመቻቸት፣ የቤቶቹን ዲዛይን በመስራትና የብድር አገልግሎት በማመቻቸት እየደገፈ መሆኑን አቶ ዓሊ አስታውቀዋል።

በቀጣይም በማህበር ለተደራጁ ሠራተኞችና ነዋሪዎች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ወደ ሀገር ቤት የገቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቤቶች ገንብተው በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪዎች የሚያከራዩበት አሠራር መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩ በተጨማሪ 524 መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም ኃላፊው አመልክተዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ከ1996 ወዲህ ከ3 ሺህ 200 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች መከፋፈላቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም