ቀጥታ፡

አዲሱ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ለስራ ኃላፊዎች ሹመት ሰጡ

ጂግጅጋ ነሀሴ 23/2010 የሶማሌ ክልላዊ መንግስት አዲሱ  ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስተፌ መሐሙድ የክልሉን ልዩ ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ለአስር የስራ ኃላፊዎች ሹመት ሰጡ፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ሹመቱን የሰጡት ቀደም ሲል የነበሩት የስራ ኃላፊዎች በክልል ተከስቶ ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ክፍተት አሳይተዋል ተብለው በመነሳታቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህም የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋጋት ለሚደረገው ጥረት ህግና ስርዓትን ለመመለስ አዲስ የተሾሙት የስራ ኃላፊዎች ዝርዝር የሚከተሉት ናቸው፡፡ 1/ ሻለቃ መሀመድ አብዲ የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ እና  ምክትላቸውን ደግሞ ሻለቃ ሐሰን  አብዲ፣ 2/ የልዩ ኃይል አስተዳደር ኃላፊ አቶ በሼር አው ሀሰን፣ 3/ የሎጀስቲክ ኃላፊ ኮሎኔል ጀርመኔ ሙሁመድ፣ 4/የመረጃ ኃላፊ ሻለቃ ሙክታር ሼክ ሁሴን ፣ 5/ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሀመድ ዓሊ እና   ምክትላቸው ደግሞ መሐመድ አብዲ፣ 6/የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ኮሎኔል አብዲከሪም ሼህ ሙሴ 7/ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ አቶ  ኡመር ዶል ሂርስ እና 8/የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከደር አደም  ሆነው በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መሾማቸውን የክልሉን ቴሌቭዥን / ኢኤስ ቲቪ/ በምንጭነት ጠቅሶ ሪፖርተራችን ከጅግጂጋ ዘግቧል፡፡ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ነሐሴ 20/2010ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ሙስተፌ መሀሙድ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አድረጎ መሾሙን በወቅቱ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም