በሀገሪቱ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

128

አርባ ምንጭ፣ ጥር 14/2014 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአርባ ምንጭ የተዘጋጀው ክልል አቀፍ የእንሰሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ንቅናቄ መድረክ ተጠናቋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ የዝርያ ማሻሻያ ስራው 3 ነጥብ 5 በመቶ ላይ ይገኛል።

እንደ ሀገር ይህን ለማሳደግ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያ፣ የኮርማ ዘረመልና ናይትሮጂንን ተደራሽ ለማድረግና የመኖ ልማትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ዶክተር ፍቅሩ እንዳሉት እስካሁን በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት እየተገኘ ሲሆን፤ በደቡብ ክልል በዝርያ ማሻሻል 6 ነጥብ 8 በመቶ ላይ ደርሷል።

የክልሉን ተሞክሮ በሁሉም ክልሎች ለማስፋት እየተስራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ዓመት ብቻ 6 ሺህ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው ጊደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ በክላስተር ለተደራጁ አርሶና አርብቶ አደሮች መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ይህም ከፍተኛ የወተት ምርት የሚሰጡ ላሞች ቁጥር እንዲጨምር የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለውም አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ዓመት አደአ ወረዳ ዲንካካ ቀበሌ በወተት ሀብት ልማት በክላስተር ለተደራጁ አርሶ አደሮች 148 የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው ጊደሮች ቀርበው ከ147ቱ ጥሩ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

ይህን ተሞክሮ በመውስድ አደአ በርጋ ክላስተር 150 የቦረና ጊደሮች እንዲዳቀሉ በማድረግ 91 በመቶ የሚሆኑት ውጤት ማስገኘታቸውን አስረድተዋል።

የዝርያ ማሻሻል ስራውን ለማስፋት ፕሮጀክት ተቀርፆ በየደረጃው ድጋፍ እየተሰጠ ይገኛልም ብለዋል።

ለዘርፉ ተግዳሮት የሆነውን የእንስሳት መኖና ግጦሽ እጥረት ለማቃለልም የተሻሻለ መኖ ልማት እየተካሄደ ሲሆን፤ የሰብል ተረፈ ምርትንም ለእንስሳት መኖ ለማዋል እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ እየተሰራ ያለው ስራ በተለይ ድርቅ ሲያጋጥም ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ ስላልሆነ በቀጣይ በየደረጃው ያለው አመራር የተሻለ ስራ ለማከናወን በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም