ፎረሙ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል

108

ጥር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ አስተዳደር የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንደሚያጎለበት የታመነበት 'የሴት አመራሮች ፎረም' ዛሬ ተመስርቷል።

በከተማዋ ያለውን የሴት አመራሮች ውሳኔ አሰጣጥ ሂደትና የፎረሙን ምስረታ የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ፣ የሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የመዲናዋ አስተዳደር ከለውጥ በኋላ ለሴቶች የተለያዩ የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች መስጠቱን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ተናግረዋል።

ነገር ግን አሁንም አቅሙና ብቃቱ ያላቸውን ሴቶች ወደ ውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ሴቶች በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ጥሩ አፈጻጸም እንደሚያሳዩ ገልጸው፣ አሸባሪው ህወሓት የደቀነውን የህልውና አደጋ በመቀልበስ ረገድ ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሃና የሺንጉስ በበኩላቸው በከተማዋ የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ለማሳደግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በዋና ዋና የስራ ዘርፎች ሴቶች በአመራርነት ተመድበው ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን በመግለጽ ፎረሙ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡና ይበልጥ ውጤታማም እንዲሆኑ ያግዛል ነው ያሉት።

ሕዝቡም አመራር ሴቶችን በማበረታታትና በማገዝ በርካቶች ወደፊት እንዲመጡ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የፎረሙ አባላት በቅንጅት በመንቀሳቀስ አርዓያ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።

በቢሮው የሴቶች ዘርፍ አደረጃጀት ኃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አራጋው ፎረሙ ሴት አመራሮች የካበተ ልምዳቸውን አንዲለዋወጡና እርስ በእርስ እንዲማማሩም ያግዛል ብለዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን የሴት አመራሮችን የማስፈጸም አቅም ማጎልበትና በመደጋገፍ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ ያስችላቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የሴት አመራሮች ፎረሙ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃም እንደሚደራጅ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም