አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውሃ የልህቀት ማዕከልነት የትምህርትና ምርምር መርሃግብሮቹ ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውሃ የልህቀት ማዕከልነት የትምህርትና ምርምር መርሃግብሮቹ ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13/2014(ኢዜአ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውሃ የልህቀት ማዕከልነት በሚተገብራቸው የትምህርትና ምርምር መርሃ ግብሮች ዓለም አቀፍ እውቅናን አገኘ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እውቅናውን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ የውሃ ማኔጅመንት የልህቀት ማዕከል በሥሩ ሦስት የሦስተኛ ዲግሪ እና በድህረ-ምረቃ አምስት መርሃግብሮችን በመተግበር የሰው ኃይል አቅሙን እያሳደገ ነው።
በዚህም በውሃው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ በምርምሩም አዎንታዊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
ፕሮፌሰር ጣሰው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በመስኩ ባከናወናቸው ተግባራት በጀርመን አገር ኮሎኝ ከተማ ከሚገኝ ዓለምአቀፉ የጥራት ማረጋገጫ ኤጀንሲ እውቅና አግኝቷል።

ዩኒቨርሲቲው እውቅና ያገኘው በርካታ መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ጠቅሰዋል።
እውቅናው ዩኒቨርሲቲው በዓለምና በአፍሪካ ደረጃ ታዋቂ ባለሙያዎችን ለማፍራት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው የተመረጠበትን መስፈርት ሲያብራሩም የሥርዓተ ትምህርቱ ተግባር ተኮር መሆን፣ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለው ቅንጅት፣ የማስተማሪያ ክፍሎች ሙሉነትና ዝግጅትን ጠቅሰዋል።
የተማሪዎችና የመምህራን ችሎታ ግምገማ ኤጀንሲው ከግምት ያስገባቸው ሌሎች ጉዳዮች መሆናቸውንም ነው ፕሮፌሰር ጣሰው ያብራሩት።
በልህቀት ማዕከሉ ከአፍሪካ በርካታ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል ማግኘታቸው በግምገማው መካተቱን ጠቅሰው፤ ተማሪዎች የሚያገኙት አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀ መሆኑም ታይቷል ብለዋል።
እውቅናው የሚቆየው ለአምስት ዓመት መሆኑን ያስረዱት ፕሮፌሰሩ፤ ከአምስት ዓመት በኋላ ዩኒቨርሲቲው ያለበት ደረጃ እንደገና ተገምግሞ እውቅናው ሊታደስም ሊነጠቅም ይችላል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም ታይምስ ሃየር ኤጁኬሽን ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ደረጃ አውጪ ተቋም ከ1 ሺህ 600 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ 402ኛ ደረጃን ማግኘቱ ይታወሳል።