የክልሉ ህዝብ ከህልውና ትግሉ ባሻገር በልማቱም ላይ ንቁ ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

93

አዳማ፤ ጥር 13/2014 (ኢዜአ) የክልሉ ህዝብ የሀገሩን ህልውና ለማስጠበቅ እየሰጠ ካለው ድጋፍ ባሻገር በልማቱ ላይ ንቁ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ በአዳማ ከተማ በህዝብ ተሳትፎና ባለሃብቶች እየተገነቡ ያሉ  የአብዲ ቦሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን  ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጉብኝተዋል።

በዚህ ወቅት አቶ  ሽመልስ፤ የክልሉ የትምህርት ጥራት ችግር በቅድመ መደበኛ የትምህርት ፕሮግራሞችና ልማት  ላይ  ያለመስራቱና አሁንም መፍታት ያልተቻለ የሴክተሩ ማነቆ ነው ብለዋል።

የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ከታች ጀምሮ ትውልዱን በመቅረጽ ጥራት ለማምጣት አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተመልክቷል።

በዚህም በክልሉ በህዝብ ፣ በባለሃብቶችና የተለያዩ ድርጅቶች ተሳትፎ ግንባታቸው ከተጀመሩ 3ሺህ 100 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እስካሁን 2ሺህ 612 የሚሆኑት አጠናቀን ለአገልግሎት ዝግጁ አድርገናል ብለዋል።

በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን፣  ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች፣ ፣አነስተኛ የመጠጥ ውሃና ለሌሎችም የልማት ስራዎች   የክልሉ ባለሃብቶችና ህብረተሰቡ ከ36 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

በቀጣይ ዓመት ተጨማሪ 4ሺህ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እንጀምራለን ያሉት አቶ ሽመልስ፤  የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን  ቁጥር በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ከ12ሺህ በላይ ለማድረስ አቅደን ርብርብ እያደረግን ነው ብለዋል።

የጀመርነው ሁሉን አቀፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ፈጥነው እንዲጠናቀቁ የክልሉ ህዝብ የሀገሩን ህልውና ለማስጠበቅ እየሰጠ  ካለው ድጋፍ  ባሻገር በልማቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉ የሚመሰገን ነው ያሉት።

አሁንም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉዞአችን በጅምር ላይ በመሆኑ ሁላችንም ባለን አቅም፣ጉልበትና የገንዘብ ተሳትፏችንን አጠናክረን በማስቀጠል የክልሉና የሀገራችን ብልፅግና ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።

በክልሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ልማት ለማከናወን ስትራቴጅ በመቅረፅ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ናቸው።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ  ብቻ ከ2ሺህ 600 በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በመገንባት ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ባለሃብቶች፣ድርጅቶችና ከመላው ህብረተሰብ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ  መደረጉን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የቅድም መደበኛ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ፕሮግራም ለማስጀመር ከ3ሺህ በላይ መምህራን አስልጥኖ ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ በግንባታ ላይ ያሉት ትምህርት ቤቶች  ማጠናቀቅና በመማሪያ ቁሳቁስ የማደራጀት ስራ ቀጣይ ተግባራችን ነው ብለዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤  የከተማዋ ባለሃብቶች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ አራት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እየገነቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የዲዛይን፣የክትትልና የቁጥጥር ስራ በማከናወን የተሻለ አፈፃፀም ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የከተማዋ ህዝብ ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ በራሱ በማሰባሰብ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም