ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የታክስና ጉምሩክ ባለሙያዎች ማህበርን ለመመስረት እንቅስቅቃሴ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ ነሀሴ 23/2010 የኢትዮጵያ የታክስና ጉምሩክ ባለሙያዎች ማህበርን ለመመስረት እንቅስቅቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተጠቆመ። የማህበሩ ምስረታ እንዴት እውን ይሁን በሚለው ዙሪያ ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት ተካሄዷል። የማህበሩ መመስረት ሀሳብ አፍላቂና የ'አፍሮ ግሎባል' አማካሪ ድርጅት ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍሰሃጽዮን መንግሥቱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያለው "የታክስና ግብር  አሰራር የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እያመጣ አይደለም"። 'ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሥራው በመንግሥት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ በመሆኑ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ የማህበሩ መመስረት በዚህ ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። ማህበሩ በአቅም ግንባታ ዙሪያ ድጋፍ መስጠት ፣ ጥናት አካሄዶ ለችግሮች መፍትሄ መስጠት እንዲሁም የታክስና ግብር ህጎችና መመሪያዎች ሲወጡ መንግሥትን በማማከር ዘርፉ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ያራሱን አሻራ እንደሚያሳርፍም ነው ያብራሩት። የህግ ግልጽነት አለመኖር፣ የአቅም ማነስ ችግርና ኀብረተሰቡ ስለ ታክስ ያለው ግንዛቤ በቂ አለመሆን በመስኩ የሚጠበቀው ውጤት እንዳይመጣ ማደረጉን የገለጹት ፕሮፌሰር ፍሰሃፂዮን፤ ማህበሩን የምናቋቁመው ከመንግሥት ጋር በችግሮቹ ለመስራት ነው ብለዋል፡፡ የማህበሩን መመስረት ተከትሎም መንግሥትን በምን መልኩ እንደግፍ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ኮሚቴ ይቋቋማል ብለዋል ፕሮፌሰሩ። ''አገር የሚገነባው በሁለትና ሦስት ሰው አይደለም'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ለማህበሩ መመስረት ቀና ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ እስካሁን 120 በለሙያዎች በአባልነት የተመዘገቡ ሲሆን ባለሙያቹ ከታክስ ፖሊሲ፣ ከታክስ ህግና አስተዳደር፣ ከጉምሩክና ታክስ አካውንቲንግ ዘርፍ የተውጣጡ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመጡት አቶ ዮሃንስ ወልደገብርኤል በበኩላቸው "ታክስ የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት አይደለም የሁላችንም ነው፤ ማህበሩ ደግሞ  የሚደገፈው ነው" ሲሉ ገልጸዋል። የታክስ አሰራሩ በባለሙያ የታገዘ መሆን ይገባዋል፤ በዚህ በኩል ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት በኩል ደግሞ ማህበሩ ያራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት እንዳለቸውም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም