ጋናዊቷ ሞዴል ዶክተር ሴተር ኖርግቤ የተደነቀችበት የኢትዮጵያ ጥምቀት - ኢዜአ አማርኛ
ጋናዊቷ ሞዴል ዶክተር ሴተር ኖርግቤ የተደነቀችበት የኢትዮጵያ ጥምቀት
ጥር 13/2014 /ኢዜአ/ ጋና ውስጥ በተካሄደ የቁንጅና ውድድር ስለኢትዮጵያ ታሪክና መልካም ገፅታዎች ባቀረበችው ንግግር አድናቆት የተቸራት ጋናዊቷ ሞዴል ዶክተር ሴተር አብራ ኖርገቤ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገች ነው።
የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋ ሴተር ከትናንት በፊት የተከበሩትን የከተራና የጥምቀት በዓላት በአዲስ አበባና ባቱ(ዝዋይ) በመገኘት አስገራሚውን የታቦታት ጉዞና የበዓል አከባበር ተመልክታለች።
ስለጥምቀት በዓል አከባበርና ቀልቧን ስለሳቡ ጉዳዮች ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገችው ዶክተር ሴተር፥ "ጥምቀትን ስመለከት ይህ የመጀመሪያዬ ነው፤ በዓሉ እጅግ አስደናቂ ነው" ብላለች።
የከተራን በዓል በአዲስ አበባ የጥምቀትን ደግሞ በባቱ( ዝዋይ) በመገኘት የታደመችው ሴተር፥ ህዝቡ በነቂስ ወደ አደባባይ ወጥቶ ታቦታቱን የሚያጅቡበትና የታቦታቱ ኡደት እጅጉን ቀልቤን ስቦታል ነው ያለችው።
“ጥምቀት እጅግ አስገራሚ ነው፤ በቀደም ከተራን በአዲስ አበባ አክብሪያለሁ፤ አሁን ደግሞ ዝዋይ ነኝ፤ አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ህዝብ ወጥቶ መንገዱ ሁሉ ተጨናንቆ በዓሉ እጅግ ደማቅ በሆነ መንገድ ሲያከብር አይቻለሁ፤ ጥምቀት በሐይቅ ላይ ሲከበር ደግሞ በዝዋይ(ባቱ) ላይ ተገኝቼ አይቻለሁ፤ ይህ ለኔ የመጀመሪያዬ ነው፤ ታቦታቱ በሐይቁ ላይ ሲጓዙ ያየሁበት ትዕይንት እጅግ አስደንቆኛል፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ፣ የበዓሉ ማድመቂያ ፊኛዎች ቀልብ ይስባሉ፤ ሁሉም ነገር አስደሳችና አስገራሚ ነበር ለኔ።ህፃናት ታቦታቱን ለመቀበል ሃይማኖታዊ ልብስ ተጎናፅፈው በዝማሬ ሲጓዙ ያየሁት ትይንትም ገራሚ ነበር” ብላለች።
ጋናዊቷ ዶክተር ሴቶር ኖርግቤ በሀገሯ ጋና በተካሄደው የቁንጅና ውድድር ኢትዮጵያ የሰው ዘር የበርካታ የቱሪስት መስህብ መገኛ መሆኗን አስተዋውቃለች።