ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግስት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው

ጥር 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ያለውን ጥረት የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ አደነቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ እና በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ ሚኒስትሯ ቪኪ ፎርድ ሀገራቸው የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ወዳጅ መሆኗን ተናግረው፤ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እየሰራች መሆኗን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ መንግስት ሰላም እንዲሰፍን በሚያደረገው ጥረት ወደ ትግራይ ክልል መከላከያ ሠራዊት አሰማርቶ ዘመቻ ላለማድረግ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉን አሳታፊ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ እና በቅርቡ እስረኞችን መፍታቱ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተሳተፉ አካላት አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ለጥፋታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከተመድ አቻው ጋር ስላደረገው ምርመራም አንስተው ተወያይተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው መንግስት ሰብአዊ ርዳታ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል እያደረገው ያለውን እንቅስቃሴ አብራርተዋል።

መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅች እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖች ወደ መቀሌ በእየዕለቱ በረራ እንዲያደርጉ ፍቃደኛ ነው ብለዋል ።

ሚኒስትር ዴኤታው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከአሁን በፊት ለሰላም የተዘረጉ በርካታ አማራጮችን ማምከኑን አንስተው አብራርተዋል።

የሽብር ቡድኑ የቀውሱ ጠንሳሽ መሆኑን እና በኋላ ላይም መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ ሲል ያሳለፈውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደ ጎን በማድረግ ቀውሱን ወደ ሌሎች ክልል እንዲስፋፋ አድርጓል ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ አሁንም የሰብአዊ እርዳታ ሂደቱን ለመረበሽ በአፋር አብአላ በኩል የጥቃት እየፈፀመ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የተመደበውን ነዳጅ ለሌላ ተግባር እያዋለ እና የአሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ እየረበሸ ነው ብለዋል ።

አምባሳደር ሬድዋን በንፁኃን ላይ የሰው አልባ የአውሮፕላን ጥቃት እየተፈፀመ ነው የሚለው መረጃ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ያሉ ሲሆን:የሽብር ቡድኑ አሁንም በአጎራባች ክልሎች ጥቃት መፈጸሙን አላቆመም ነው ያሉት።

አምባሳደር ሬድዋን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ ተደራሽነቱን አንድ አካባቢ ብቻ ማተኮሩን ትቶ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው ሁሉም አካባቢዎች እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሓት የሽብር ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈፀመውን የሽብር ጥቃት ሊያወግዝ ይገባል ነው ያሉት።

እንግሊዝ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያሳየችውን ፍላጎት አድንቀው፣ የኢትዮጵያ ወሳኝ የልማት አጋር መሆኗንም ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡

ምንጭ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም