የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

65

ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 12/2014---በፀጥታ ችግር ምክንያት ለጎብኚዎች ዝግ ሆኖ የቆየው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ዛሬ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ በይፋ ሥራ ጀመረ።

በአማራ ክልል በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የቱሪስት መዳረሻዎች ወደቀደመ እንቅስቃሴአቸው ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውም ተመላክቷል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሽለሺ ግርማ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለጎብኚዎች ከፍት ሆኖ ሥራ መጀመሩን በይፋ አብስረዋል።

አቶ ሽለሺ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ በፀጥታ ችግር ምክንያት ለጎብኚዎች ዝግ የነበሩት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች ክፍት ሆነዋል፡፡

በክልሉ በገና እና በጥምቀት በዓላት ላይ ለመታደም የመጡ በርካታ ዳያስፖራዎች እነዚህን ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦችን እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፣ በቱሪስት መዳረሻዎቹ ጎብኚዎች ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙ ሆቴሎች፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ አስጎብኚዎችና መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ የማድረግ ሥራዎችም ተከናውነዋል።

በአካባቢው በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ሳቢያ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለጎብኚዎች ዝግ ሆኖ መቆየቱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል።

በዚህም በተያዘው ሳምንት ብቻ ከ20 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ፓርኩን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ላለፉት ሦስት ዓመታት በኮቪድ እና በፀጥታ ችግር ምክንያት ወደፓርኩ ቱሪስቶች ባለመምጣታቸው ከ10 ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቱሪዝም ተጠቃሚነት ተገለው ቆይተዋል፡፡

በደባርቅ ከተማ በአስጎብኚነት ሥራ የተሰማራው ወጣት መኳንንት መሳፍንት እንዳለው ፓርኩ ለጎብኚዎች ክፍት በመደረጉ መደሰቱን ጠቁሞ፣ ቱሪስቶችን ለማስጎብኘት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

እንደ አውሮፓወያን የዘመን አቆጣጠር በ1978 በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የሌሎች በርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑም ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም