ቀጥታ፡

ቻይና ለኢትዮጵያ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ 19 ክትባት ድጋፍ አደረገች

ጥር 12/2014/ኢዜአ/ ቻይና ለኢትዮጵያ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ 19 ክትባት ድጋፍ አደረገች።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛዎ ዚዩሃን እና የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የድጋፍ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።   

ድጋፉ ቻይና የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ ቃል መግባቷን ተከትሎ የተደረገ እንደሆነ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተመልክቷል።  

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የቻይና መንግሥት ከዚህ ቀደምም ለአራት ተከታታይ ጊዚያት የሲኖፋርም ክትባት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።  

የአሁኑ የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ድጋፍ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸው ይህም ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ክትባትን ተደራሽነት ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።  

የቻይና መንግስት እስካሁን 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማደረጉን የተናገሩት ሚኒስትሯ ለዚህ ያልተቋረጠ እገዛም የኢትዮጵያ መንግስት ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ከጤናው ዘርፍ ባለፈ በሌሎችም መስኮች ያላቸው ትብብርና አጋርነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይገኛል ሲሉም አክለዋል።   

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛዎ ዚዩሃን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደግፋለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ50 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም