ኢትዮጵያ በቀጠናዊ የንግድ ትስስር ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ ነው -ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቀጠናዊ የንግድ ትስስር ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ ነው -ሚኒስቴሩ
አዳማ ጥር 12/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቀጠናዊ የንግድ ትስስር ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆንና በሌላ በኩል ደግሞ ከምስራቅ፣ ከደቡብና ምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም ከሰሜኑ የአህጉሪቱ ክልል ጋር በንግድ እንድትተሳሰር እየተሰራ ነው።
ኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ የተቀመጡ ዘርፈ ብዙ መመዘኛዎችን የማሟላት እንዲሁም አቅምና እውቀት ጭምር የመገንባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃ የንግድ ቀጠና አባል ለመሆን የሚያስችላትን የራሷን አሰራርና የህግ ማእቀፎችን በማሻሻል የአባልነት ፊርማ ተፈርሞ ሰነዱ ለአፍሪካ ህብረት እንዲቀርብ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለገበያ የምታቀርባቸው ምርቶችና ዋጋ የመለየት በተለይም ሀገሪቱ በነፃ የንግድ ቀጠና ውድድር ውስጥ ተገቢውን ጥቅም የምታገኝባቸው ምርቶችና እቃዎችን የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል ።
በተለይም በምስራቅና ደቡባዊ የንግድ ቀጠና ላይ የኢትዮጵያ ምርቶች የገበያ መዳረሻና የመወዳደር ዕድልን ለማስፋት በነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ እንዲታይ በማድረግ በማዕቀፉ ውስጥ ካሉት ዘጠኝ ሀገሮች ጋር የማወዳደርና ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የድንበር ላይ ንግዶች ስርዓት እንዲይዙና የሁለትዮሽን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲተገበሩ በጋላፊና ሞያሌ ላይ ያሉ አሰራሮችን የማዘመንና ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሌሎች ሀገራት ጋርም ተመሳሳይ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በአጠቃላይ ከዓለም ባንክ በብድር በተገኘ 60 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጄክት ተቀርፆ ቀጠናዊ ትስስሩን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ማሻሻዎች እየተሰሩ ነው።
"በቀጠናዎች ትስስር ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ ከጎረቤት ሀገራት ጀምረን ብዙና ሰፋፊ ስራዎች እየሰራን ነው" ያሉት ደግሞ የንግድና ቀጠናዎች ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን ሙሐመድ ናቸው።
ስትራቴጅክ እቅድ ከመቅረፅ ባለፈ ዓመታዊ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በየሩብ ዓመቱ በስራ ሂደቶች የመገምገም፣ የመፈተሽና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የማስቀመጥ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
"ከሶማሊ ላንድ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ ጋር ጠንካራ የሁለትዮሽ ትስስር እንዲፈጠር እየሰራን ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በቀጣይ ወደ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጭምር ቀጠናዊ ትስስሩን የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
"ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ነፃ የንግድ ትስስር ውስጥ የአካባቢውን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ በስፋት ታመርታለች" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ምርቱ ወደ ጎረቤት ሀገራት በስፋት እንዲላክ የድንበር ላይ ስራዎችን የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"በተለይ ቀጠናዊ የንግድ ትስስሩ የወጣቶችን የስራ እድል አማራጮችን እንዲያሰፋ ትኩረት አድርገን እየሰራንበት ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ የራሱዋን የመወዳደር አቅምና ሚናዋን እድትወጣ የምርት ጥራት ላይ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ቡናና ሌሎች የግብርና ምርቶች እንዲሁም የቁም እንስሳት፣ ወርቅና ሌሎች ማእድናት ላይ ያተኮረ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ።