ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

ጥር 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ ቡና 578 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
አፈጻጸሙ በመጠንና በገቢ ከእቅድ በላይ መሆኑንም ነው ባለስልጣኑ የገለጸው፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዘርፉ በተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ ምክንያት ባለፉት ሶስት ዓመታት የቡና ምርትና ገቢ እየጨመረ መጥቷል፡፡
የፖሊሲ ማሻሻያው በቡና ግብይት ስርዓት ውስጥ የነበረውን ስር የሰደደ ችግር በመፍታት ረገድ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱንም ነው ያነሱት፡፡በተያዘው በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸም የተሻለ ውጤት መመዝገቡን በአስረጂነት በመጥቅስ፡፡
በዘንድሮው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 148 ሺህ 882 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 578 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር በመጠን የ57 ሺህ ቶን ቡና ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው፤ ከተያዘው እቅድ አንጻር ደግሞ የ20 በመቶ የአፈጻጸም ብልጫ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በገቢ ረገድም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ274 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብልጫ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ጀርመን 37 ሺህ ቶን የኢትዮጵያ ቡናን በመግዛት ቀዳሚ ስትሆን ሳውዲ አረቢያና ጃፓን ደግሞ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል ነው ያሉት፡፡
ውጤቱ የተመዘገበው የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለአቅራቢዎች አቅራቢዎች ደግሞ ለላኪዎች እንዲያቀርቡ በተሰራው ስራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ይህም የግብይት ሰንሰለቱን ከማሳጠሩም በላይ ምርት ሳይባክንና ጥራቱን እንደጠበቀ ለገበያ እንዲቀርብ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
በተለይ ከዚህ በፊት እስከ አራት ወራት ይወስድ የነበረውን የቡና ግብይት ወደ አንድ ወር ማሳጠር መቻሉ ለምርትና ገቢ ማደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አውስተዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 280 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እሰራች መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አዱኛ ደበላ አብራርተዋል፡፡