የህዳሴ ግድብ የትብብር እንጂ የግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

97

ጥር 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የምትገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትብብር እንጂ የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደማይችል ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በግብርና፣ በማምረቻና በኢንዱስትሪዎች ላይ የተመሰረተ ዘመናዊ ኢኮኖሚ የመገንባት ውጥን ይዛ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሚስፋፉት የመሰረተልማት አውታሮች ውስጥ ለዜጎች የሚዳረሱት ጥራት ያላቸው የትምህርት፣ የጤና እንዲሁም የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቶች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ንጹህና ከብለት የጸዳ አካባቢ እንዲፈጠር በትጋት በመስራት የተፈጥሮ ሃብቶች እንዳይጎዱና ስነምህዳሮች እንዳይዛቡ በማድረግ የከባቢ አየር መበከል የሚያስከትላቸው ተጋላጭነቶች እንዲቀንሱ እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ህልሞች እውን የሚሆኑት ንጹህ የሃይል አቅርቦት አማራጮች ተግባራዊ ሲደረጉ መሆኑን ያሰመሩበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በለገሳት የውሃና የመልክአምድር ስጦታዎቿ ተጠቅማ ህልሟን እውን ለማድረግ ጥረት እያደረገች እንደሆነ ገልጸዋል።

አብዝታ ልትጠቀምባቸው ከምትችላቸው መስኮች መካከል የታዳሽ ሃይል ዘርፉ ቀዳሚው ቢሆንም ከ53 በመቶ አሊያም ከ60 ሚሊየን በላይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ከኤሌክሪክ ሃይል ጋር አይተዋወቁም ብለዋል።

ያለኤሌክትሪክ ሃይል የትኛውም አገር ድህነትን አላሸነፈም አካታች እድገትን አላረጋገጠም የዜጎቹን ኑሮ አላረጋጋም እንዲሁም ዘላቂ የኢኮኖሚ የማህበራዊና የአካባቢ ልማት ስኬቶችን አላስመዘገበም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የአባይ ውሃ በምክንያታዊነት እና በፍትሃዊነት ጥቅም ላይ እንዲውል ያላት ፍላጎት ጽኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሉም ኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድቡም ይሄንን የኢትዮጵያን የመተባበር መርህ አጉልቶ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ከግብጽና ሱዳን ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ አገራትም ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።  

ግድቡ ሲጠናቀቅ 15 ሺህ 700 ጊጋዋት ሰዓት በዓመት የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያመነጭና 90 በመቶ የሚሆነው ሃይል የሚመረተው የኢትዮጵያን የክረምት ወቅት መሰረት በማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይሄንን የፍሰት አለመመጣጠን ለማስቀረትና ወንዙም አመቱን ሙሉ ተመሳሳይ የውሃ ፍሰትና ያልተቆራረጠ የሃይል ምርት እንዲኖረው ግድቡ በቂ ውሃ መያዝ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።  

ግድቡ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት የሚኖረው ጠቀሜታ እንዳልተነገረለትና ሱዳንን በየአመቱ ከሚያጋጥማት የጎርፍ አደጋና በበጋ ከሚፈጠረው የውሃ እጥረት ስጋት ነጻ እንደሚያደርጋት አብራርተው የግድቡ መጠናቀቅ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ከኢትዮጵያ ጋር ለተሳሰሩት ሱዳንና ሌሎች ሃገራት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።   

ከአስዋን ግድብ የሚተነውን የውሃ ሃብት በመቀነስ በአጠቃቀምና በአያያዘ ረገድ ግድቡ ለግብጽም የሚሆን ትሩፋት እንደሚኖረው አስረድተው፤ በመላው አለምና በአባይ ወንዝ ቀጣና ታዳሽ ሃይል በማምረትና በካይ ንጥረ ነገሮችን በመቀነስ ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካትና ለአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እውን መሆን ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አስገንዝበዋል።

አፍራሽ አስተሳሰቦችን ወደ ጎን በማለት ገንቢ እሳቤዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱ ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በመረዳት ሰላምን ለመገንባት አንዱ ሌላውን ሳይጎዳ ተያይዞ ለመልማት የአባይ ወንዝ እንደ አጠቃላይና የህዳሴ ግድብ በተለየ የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን በመገንዘብ  ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በጋራ መንቀሳቀስ አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም