በአዲስ አበባ 300 ሺህ ሰዎች የሚሳተፉበት የባህል ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው

86

አዲስ አበባ፣ ጥር 12/2014 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ 300 ሺህ ሰዎች የሚሳተፉበት የባህል ፌስቲቫል ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ለሶሰት ቀናት ይካሄዳል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤13ኛውን ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

የፌስቲቫሉ ዋነኛ አላማ የማህበረሰቡን ወግ፣ ባህልና በጎ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን ማስተዋወቅ መሆኑን አብራርተዋል።

በሁሉም ክልሎች የሚከወኑ ባህላዊ እሴቶች በከተማዋ በሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች ለእይታ ይቀርባሉ ብለዋል ዶክተር ሂሩት።

የብሔር ብሔረሰቦች የባህል፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ሌሎች ክዋኔዎች ለህዝብ የሚተዋወቁ መሆኑን ጠቅሰው ፌስቲቫሉ አምራቾችና ሻጮች የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩም የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ባህላዊ ምግብና መጠጦች፣ አልባሳት የዲዛይን ውድድሮችና ሌሎች ሁነቶች ይከናወንበታል ነው ያሉት።

አገር በቀል እውቀቶች እንዳይጠፉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተደግፈው ለትውልድ ማስተዋወቅና ማስተላለፍ ስለሚቻልባቸው አማራጮች ላይ የምሁራን ውይይት የሚካሄድ ይሆናል።

በፌስቲቫሉ 300 ሺህ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ሃላፊዋ ተናግረዋል።

ከጥር 15 እስከ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል በሚካሄደው ፌስቲቫል ተሳታፊዎች የአገር ባህል ልብስ ለብሰው መምጣት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው ለመጡ የዲያስፖራ አባላት በከተማዋ የተዘጋጁ ባዛርና ፌስቲቫሎች ማጠቃለያ እንዲሆን ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ዶክተር ሂሩት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም