በምንጃር ሸንኮራ በኢራንቡቲ ጥምቀት በዓል የሚገኙ ታዳሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በምንጃር ሸንኮራ በኢራንቡቲ ጥምቀት በዓል የሚገኙ ታዳሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

ጥር 12/2014 ( ኢዜአ) በምንጃር ሸንኮራ በኢራንቡቲ ጥምቀት በዓል የሚገኙ ታዳሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አስተዳደር ገለጸ።
በወረዳው ኢራንቡቲ 44ቱ ታቦታት በተገኙበት የጥምቀት በዓል ለ620ኛ ጊዜ በድምቀት ሲከበር በርካታ ምእመናንና ቱሪስቶች ተገኝተዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ቦሰት እንደተናገሩት በኢራንቡቲ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ለመሳተፍ ህብረተሰቡ ከቀደመው በተሻለ መልኩ ወደ አካባቢው በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የጥምቀት ማክበሪያ ቦታውን የማልማት ስራ መጀመሩን ጠቁመው በመንግስት በኩል መንገዶች፣ ድልድዮች እና ሌሎች መሰረት ልማቶች እየተሟሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ አስደናቂ የሆኑ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና የተፈጥሮ ሃብቶችን የቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢራንቢቲ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ከጥንት ጀምሮ እየተከበረ እስካሁንም የዘለቀ አስደናቂ ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህ ቦታ ላይ 44 ታቦታት በአንድ ላይ ሆነው የሚከበሩበትና የበርካቶችን ቀልብ የሚገዛ ልዩ የአከባበር ስርአት መኖሩን ተናግረው የማስተዋወቁ ስራ ግን እምብዛም አልተሰራም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በዞኑ የሚገኙ አስደናቂ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና የተፈጥሮ ሃብቶችን የቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በየዓመቱ የሚከበረው የጥምቅት በዓል ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ ባሻገር የኢትዮጵያ ብሎም የዓለም ቅርስ በመሆኑ በርካታ ቱሪስቶች እንዲታደሙበት እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
"በዞኑ በኢራንቡቲ እና ጋድሎ ሜዳ የሚከበሩ የጥምቀት በዓላት ልዩ ናቸው" ያሉት አስተዳዳሪው መሰረተ ልማቶችን በማልማትና ለእንግዶች ምቹ ማረፊያዎችን በማዘጋጀት ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም በኢራንቡቲ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ለየት ያለ እና ደማቅ መሆኑን ገልጸው በስፋት እንዲተዋወቅ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በአፄ ልብነ-ድንግል ዘመነ መንግስትም በደማቅ ሁኔታ ይከበር እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ።