ቀጥታ፡

የሕትመት ሚዲያ ኢንዱስትሪ መንግስት ሊታደገው ይገባል- የዘርፉ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ ነሀሴ 23/2010 ከሕትመት ዋጋና ማስታወቂያ ጋር ተያይዞ አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የሕትመት ሚዲያ ኢንዱስትሪ መንግስት እንዲታደገው የዘርፉ ባለሙያዎች ጥሪ አቀረቡ። በተለይም የግል ፕሬሱ መቃብር አፋፍ ላይ እንደሚገኝ በመጥቀስ አስቸኳይ ህክምና ያስፈልገዋልም ነው ያሉት ባለሙያዎቹ ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰሞኑን በጉዳዩ ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ መንግስት የንባብ ባህል እንዲዳብር፣ የሕትመት መገናኛ ብዙሃን እንዲጎለብት ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸው ይታወሳል። በተለያዩ የሕትመትና ብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ላይ ረጅም ልምድ ያለው አንጋፋው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እንደተናገረው  ''የኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ኢሕአዴግ ወልዶ ያላሳደገው የ1980ዎቹ ክስተት ነበር'' ይላል። ከ1984 ጀምሮ እስከ 1992 ዓ.ም ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ የሕትመት ኢንዱስትሪው የተነቃቃበት እንደነበር የሚያስታውሰው ጋዜጠኛው ጥበቡ፤ በኋላ ግን ኢንዱስትሪው መልሶ የከሰመ መሆኑን ይናገራል። መልሶ ለመክሰሙ መንስዔ የሆነው ፕሬሱ ዘላቂ የአደረጃጀትና ፋይናንስ የሌለው መሆኑ አንዱ ሲሆን በሕግ ረገድ ጋዜጠኞች ሊቋቋሟቸው የማይችሉ ክሶች መበራከት፣ ለህትመት ዋጋ መናር ኢንዱስትሪው እንዳያድግ እንቅፋት መሆናቸውን ይገልጻል። በተለይም ከ1997 ምርጫ በኋላ በተለያየ መንገድ መንግስታዊ ጫናዎች መኖራቸው በርካታ ጋዜጦች ከህትመት ለመውጣት መገደዳቸውንና ጋዜጠኞችም ለስደት መዳረጋቸውን አስታውቋል። 82 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ጀርመን በቀን ከ37 ሚሊዮን ቅጅዎች በላይ ጋዜጦች እንደሚታሙ የሚያነሳው ጋዜጠኛ ጥበቡ፣ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት አገር ኢትዮጵያ የሚታተሙት ሳምንታዊ ጋዜጦች ቁጥር ከ30 ሺህ እንደማይዘል ይገልጻል። በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ኃላፊነት ሲሳተፍ የቆየው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና በቅርቡ ከገበያው የወጣችው የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ የወረቀት፣ የቀለምና የሕትመት ዋጋ ለህትመት ሚዲያው መቀጨጭ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ የጋዜጠኛ ጥበቡን ሃሳብ ተጋርተዋል። እንደ ጃፓን ባሉ አገሮች አንድ ጋዜጣ ብቻ በቀን እስከ ስምንት ሚሊዮን ኮፒ እንደሚታተም የሚገልጸው ጋዜጠኛ ውብሸት፤ በ1997 ዓ.ም እስከ 100 ሺህ ቅጅዎች ይታተም እንደነበር ገልጾ ዛሬ ላይ ግን ይህ እድል እንኳን አለመኖሩን ይጠቅሳል። በኢትዮጵያ ያለው የማስታወቂያ ሰርዓት የግል ፕሬሱን ያገለለ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎቹ፤ የግል ድርጅቶች ማስታወቂያ ለማግኘት እንኳን የተለያየዩ ስልታዊ ጫናዎች እንደሚደረግባቸው ይገልጻሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉትም ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ባላት አገር ያለው የህትመት ሚዲያ መዳከም በንባብ ባህል ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተዕጽኖ የጎላ ነው። እናም የሕትመት ሚዲያ አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልገው ዘርፍ እንደሆነ ይጠቁማሉ። የህትመት ሚዲያ ኢንዳስትሪውን ለማሳደግና የንባብ ባህል ለማሳደግ በወረቀት ላይ የሚጣሉ ታክሶች ማንሳት፣ የህትመት ዋጋን መቀነስ፣ የሕግ ማዕቀፎችን ማስተካከል፣ ፍትሃዊ የማስታወቂያ ስርዓት መዘርጋትና በማስታወቂያ ድርጅቶችን ነጻ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በጉዳዩ ዙሪያ ከጋዜጦች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንደጠቆሙት፣ ከለውጥ በኋላ መንግስት የወሰደው ቀዳሚው እርምጃ መገናኛ ብዙኃን በነጻነት እንዲሰሩ ማድረግ ነው። ህዝቡ መረጃ የማግኘት መብቱ እንዲረጋገጥ፣ የሚጽፉና የሚያነቡ ሰዎች እንዲበዙ እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ረገድ ጥሩ እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል። የህትመት ሚዲያዎች እንዲበራከቱ እንደሚደረግ ገልጸው፤ የህትመት ሚዲያና አንባቢዎችን ለማበራከት በጥናት የተደገፈ ምላሽ እንደሚሰጥ መጠቆማቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም