ቀጥታ፡

ኃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶች ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ተሳስረው እንዲኖሩ ታላቅ ሚና እየተጫወቱ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 11/2014 (ኢዜአ )  የኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ ተቋማትና ባሕላዊ እሴቶች ዜጎችን ለዘመናት አስተሳስረው በሠላምና በአብሮነት እንዲኖሩ በማድረግ ታላቅ ሚና እየተጫወቱ ነው ሲሉ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠሩ፣ የተደራጁና የዳበሩ ባሕላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች እንዷላት ተናግረዋል።

እነዚህ ኃይማኖታዊ ተቋማትና ባሕላዊ እሴቶቿም በውስጧ የሚገኙ ዜጎቿን ለዘመናት አስተሳስረው በሠላምና በአብሮነት እንዲኖሩ ጉልህ  ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ተከባብረውና ተቻችለው አብረው በመኖር ለሌሎች አገራት ሕዝቦች አርዓያ እንዲሆኑም አድርገዋል ብለዋል።

በኃይማኖት ውስጥ ባሕላዊ እሴት አለ ያሉት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የትኛውንም ኃይማኖት የሚከተል ማኅበረሰብ ስነ ልቦናው፣ የጸሎት ዘይቤው፣ ዝማሬው፣ ዜማው፣ የሙዚቃ መሳሪያው፣ ውዝዋዜና አለባበሱ የተወለደበትን ማኅበረሰብ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

ስለዚህም የአንድ ሕዝብ ባሕልና ኃይማኖት የተሳሰሩ ናቸው ብለዋል።

ባሕላዊ እሴቶችም የፍቅርና የመቻቻል ምልክቶች ከመሆን ባሻገር ለበዓላት ታዳሚዎች የሠላምና የአንድነት መልዕክቶችን ማስተላለፋቸው ልዩ እንደሚያደርጋቸው አውስተዋል።

በኢትዮጵያ ኃይማኖት የልዩነት ምክንያት ሆኖ እንደማያውቅ ጠቅሰው ይልቁንም አንዱ የሌላውን አክብሮ፣ የደስታው ተካፋይ እንዲሆን በክብር ጋብዞ ዕለቱን በድምቀት እንደሚያከብር ጠቅሰዋል።

ይህም "ብዙ ሆነን አንድ፤ አንድ ሆነን እንደ ብዙ" አምሮብን እንድንኖርና የተለየ ውበትና ክብር እንዲኖረን አድርጎናል ነው ያሉት።

ሁኔታውን በሚገባ ያጤነው ዩኔስኮም ጥምቀትን፣ የመስቀል ደመራን፣ የገዳ ስርዓትና ፊቼ ጨምበላላ በዓላትን የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ አድርጎ መመዝገቡን አንስተዋል።

በርካታ ያልተበረዙና ያልተከለሱ ባህሎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያን ሌሎች ባሕላዊ እሴቶችም ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን እጅግ ውብ ኃይማኖታዊና ባሕላዊ ሃብቶች ለበጎ ነገር መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።    

ኃይማኖት ከመንግስትና ከፖለቲካ ድርጅት ነፃና ገለልተኛ መሆኑን ጠቅሰው የኃይማኖት ተቋማትም ነፃና ገለልተኛ ሆነው ምዕመኖቻቸውን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጪ ያጋጠሟትን ችግሮች ለመሻገር ሕዝቦቿ ባሕላዊና ኃይማኖታዊ ክንዋኔዎችን ተጠቅመው ሠላምና ዕርቅ እንዲኖር በማድረግ አገር እንድትቀጥል ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ትውፊት ዛሬም ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት፣ የኃይማኖት አባቶችም ወጣቱን በማስተማር በመልካም ስነ ምግባር እንዲታነጽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ለሠላም፣ ለእኩልነትና ለወንድማማችነት አዎንታዊ ሚና የሚጫወቱ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ለምክክር፣ ለሠላምና ለእርቅ በማዋል በመላ አገሪቷ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድም በፈጣሪም ሆነ በሰው ልጆች ዘንድ የተቀደሰ የሆነውን በጎ ተግባር በማስቀጠል ታሪክ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በዓሉ ሲከበር በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች በማገዝ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም