ከአሸባሪው ቡድን አስከፊ ቆይታ በኋላ ጥምቀትን በልዩ መንፈስ ማክበራችን ልዩ ያደርገዋል- የደሴ ነዋሪዎች

ደሴ፣ ጥር 11/2014 (ኢዜአ) ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን አስከፊ ቆይታና በደል በኋላ የጥምቀት በዓልን በልዩ መንፈስ ማክበር በመቻላችን የዘንድሮን በአል ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የደሴ ከተማ ነዋሪና የበዓሉ ታዳሚ አቶ ቢሊልኝ እሸቱ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረውን ተንኮል ለማሳካት የእምነት ተቋማት ላይ ሳይቀር ጥቃት ፈጽሟል፡፡

በደሴ ከተማ አንድ ወር ከአንድ ሳምንት በቆየበት ጊዜ ንብረት ከመዝረፍና ከማውደም ባለፈ የእምነት አባቶችን ጨምሮ በንጹሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል መፈጸሙን ገልፀዋል።

"ይሁን እንጅ በኢትዮጵያዊን የተባበረ ክንድ ከተማችን ነጻ ወጥታ አንድነታችንን ጠብቀን ለዛሬው ቀን በቅተናል"  ያሉት አቶ ቢሊልኝ "ጥምቀትን እናከብራለን ብለን ባናስብም በፈጣሪ እገዛ ዛሬ በልዩ ሁኔታ ማክበር ችለናል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ከአሸባሪው ወራሪ ሀይል አስከፊ ቆይታና በደል በኋላ ጥምቀትን በልዩ መንፈስ ማክበር መቻላችን የዘንድሮን በአል ልዩ ያደርገዋል" ብለዋል።

''ከሽብር ቡድኑ ግፍና መከራ በኋላ ጥምቀትን በአንድነት እያከበርን  ነው'' ያለው ደግሞ ሌላው ወጣት ሚኒሊክ ሞላ ነው።

"ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር በመተባበር በአሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ እየሰራን መሆኑም በአሉ የህዝቦች አንድነት መገለጫነቱን ያሳየ ነው" ያለው ወጣት ሚኒሊክ በክብረ በአሉ ስነ ስርዓት የማስከበርና አቅመ ደካሞችን የማገዝ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

በአሉ ከከተራው ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየተከበረ መሆኑን ጠቁሞ "በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን እየተወጣን ነው" ሲል ገልጿል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የደሴ ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ጠቢባን ሲራክ መለሰ በበኩላቸው ጥምቀት ሐይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በፍቅርና በአንድነት እንዲከበር በቅንጅት በተደረገ ዝግጅት በአሉ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

"በተለይ የእስልምና እምነት ተከታይ እህት ወንድሞቻችን በዓሉ የሚከበርባቸውን አካባቢዎች ከማጽዳት ጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ እያደረጉት ያለው እገዛ የወሎን የአንድነትና የመከባበር ባህልና እሴት በተግባር ከማሳየቱም ባለፈ አንድነታችንን ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ አድርጓል" ብለዋል፡፡

አሁን ላይ 21 ታቦታት ከአደሩበት ሆጤ ስታድየም ወደየ አድባራቸው በሐይማኖታዊ ስነ ስርዓት እየተሸኙ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም