በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር ዓለም የሚያደንቀውና የሚጎበኘው እሴት ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር ዓለም የሚያደንቀውና የሚጎበኘው እሴት ሆኗል
ጥር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር ዓለም በአንክሮ የሚመለከተው፣ የሚያደንቀውና የሚጎበኘው እሴት መሆኑን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
ዶክተር ሂሩት በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በዓሉ ካሉት ሌሎች ሚስጥራት በተጨማሪ ክርስቶስ በልደት በትህትና በከብቶች በረት እንደተወለደ ሁሉ በጥምቀቱም በዮርዳኖስ ወንዝ ተገኝቶ በሰው እጅ የተጠመቀበትና ለሰው ልጆች ሁሉ በድጋሚ ትህትና እና ፍቅርን ያስተማረበት ነው ብለዋል።
የበዓሉን ታሪካዊ ትውፊት በመከተል የእምነቱ ተከታዮች በትህትና፣ በጥሩ ስብዕና እና በፍቅርና ፈጣሪን በማመስገን በአደባባይ የሚያከብሩት መሆኑን ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል አከባበር ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ እሴት ሲሆን ከእኛ አልፎ የዓለም ህዝቦች ሁሉ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል።
በመሆኑም ዓለም በአንክሮ የሚመለከተው፣ የሚያደንቀውና የሚጎበኘው በዓል ለመሆን በቅቷል ሲሉ ገልጸዋል።
በዓሉ ካለው መንፈሳዊ ትርጓሜ በተጨማሪ የአገር ምጣኔ ሃብት ምንጭ በመሆኑ በተለመደው የእንግዳ አቀባበል ባህል የበዓሉ ታዳሚዎችን ማስተናገድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የጥምቀት በዓል ስርዓቱን ጠብቆ እዚህ እንዲደርስ አበርክቶ ያደረጉ ወገኖች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ቀደምቶች በዓሉ የሚያዘውን ፍቅርና ትህትና፣ ህብረትና መተሳሰብን፣ መረዳዳትና መደጋገፍን፣ ቱባ ባህልና ጥበብን እንዲሁም ሌሎች በርካታ የመልካም ስነ-ምግባር መገለጫዎችን አስረክበው ማለፋቸውን አስታውሰዋል።
የአሁኑ ትውልድም እንደ ቀደምቶቹ ሁሉ በዓሉን በመንከባከብና እሴቱን በመጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር አለበት ያሉት ዶክተር ሂሩት፤ መንግስት በልዩ ትኩረት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዓላት ሲከበሩ ኃይማኖታዊ አስተምህሮውንና እሴቱን መሰረት በማድረግ እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ እንዲሁን ጠይቀዋል።
በጃን ሜዳ በተከበረው የጥምቀት በዓል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የእምነቱ ተከታይ ምዕመናት እና ከተለያዩ አገሮች የመጡ ቱሪስቶች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼