የጥምቀት በዓል የህዝቡን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶችን የያዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓል የህዝቡን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶችን የያዘ ነው
ሐዋሳ ፤ጥር 11/2014 (ኢዜአ)፡ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ ባሻገር የኢትዮጵያዊያንን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶችን መያዙን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሲዳማ ሀገረ ስብከት አስታወቀ።
በሐዋሳና በሚዛን አማን ከተማ የጥምቀት በዓል እየተከበረ ነው ።
የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ ባስተላለፉት መልዕክትና ቃለ ምዕዳን የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ ባሻገር የኢትዮጵያዊንን አንድነትና ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶችን የያዘ ነው ።
በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው ጥምቀት ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ትውፊቶቹ ተጠብቀው እንዲቀጥሉ መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል።
"ሀገር ከቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘው ጥቅም እየጎለበተ እንዲሄድ አብሮታችንንና መተሳሰባችንን አጎልብተን የምንገልፅበት ሊሆን ይገባል" ብለዋል ።
ከከፋፋይ ሀሳቦች ይልቅ እርስ በእርስ ለሚያስተሳስሩና ለሚያቀራርቡ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት አንድነትን ማጽናት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሚልኪያስ በትሬ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ክዋኔው ባሻገር ለከተማዋ ድምቀትና ለቱሪዝም እንቅስቃሴው ማደግ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮቶቿ ለሀገር ሠላምና ለህዝቦች አንድነት የምታደርገው አበርክቶ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በሠላም ግንባታና በፀጥታ ሥራዎች ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር የሚያደርገውን የተቀናጀ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በሐዋሳ ከተማ ደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እየተካሄደ ባለው የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ ሌሊት በማህሌትና ቅዳሴ ሥርዓት እግዚአብሔርን ሲያመሰገኑ ያደሩት የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የክርስቶስን ጥምቀት የተመለከተ ያሬዳዊ ጥዑመ ዜማ አቅርበዋል ።
በተመሳሳይ ሁኔታ በዓሉ በሚዛን አማን ከተማ የሁሉም አድባራት የቃል ኪዳን ታቦታት ወደ ወንዝ ወርደው በማደር ጠዋት ላይ የጥምቀት መርሃ ግብር ተካሂዷል።
ወጣቶች ከምንጣፍ ማንጠፍና የምስጋና አገልግሎት ባሻገር ከከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ መዋቅር ጋር በመሆን በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ እንዲሆን እየሰሩ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ በአሉ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ላይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተከበረ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች እያሳዩ ያሉትን ተግባር አድንቀዋል።