ምዕመናን ጥምቀትን የአብሮነት እሴቱንና አንድነቱን በማጠናከር ሊያከብሩ ይገባል

9

ጋምቤላ፣ ጥር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምዕመናን የጥምቀት በዓል አብሮነትና አንድነትን በማጠናከር እንዲያከብሩት የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል፣ የምዕራብ ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሩፋኤል አሳሰቡ።

የከተራ በዓል በጋምቤላ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።

አቡነ ሩፋኤል በክብረ በዓሉ ላይ እንዳሳሰቡት ምዕመናን በዓሉን እርስ በርስ በመደጋገፍና በመተሳሰብ ሊያከብሩት ይገባል።

ምዕመናን ጥምቀት ሰላም፣ አንድነት ፍቅርና ነፃነት መሆኑን በመገንዘብ አቅም የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍ እንዲያከብሩትም አስገንዝበዋል።

የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ ያሳየውን መልካም ተግባር እንዲያጠናክር አቡነ ሩፋኤል ጠይቀዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የጥምቀት በዓልን የእርስ በርስ መደጋገፍና የመረዳዳት ባህሉን በመጠበቅ እንደሚያከብሩት ገልጸዋል።

የቆየ አንድነትና አብሮነትን በማደስ በዓሉን በፍቅር እንደሚያከብሩትም ጠቁመዋል።

በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው በምዕመናን ታጅበው በባሮ ወንዝ በተዘጋጀው ከተራ ቦታ ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም