በዓሉ ሲከበር ከጥላቻ በመራቅ በቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ መሆን ይገባል -ብፅዑ አቡነ አብረሀም - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉ ሲከበር ከጥላቻ በመራቅ በቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ መሆን ይገባል -ብፅዑ አቡነ አብረሀም

ባህር ዳር ጥር 10/2014 (ኢዜአ ) ምዕመናኑ የከተራና የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ከጥላቻ በፀዳ መንገድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና አስተምህሮ በሚገልጽ መልኩ መሆን እንዳለበት የባህር ዳር ሀገር ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፅዑ አቡነ አብረሀም አሳሰቡ።
የከተራ በዓል በባህር ዳር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
ብፁዕነታቸው በከተራ በዓል አከባበር ላይ ባስተላለፉት መልእክት ሀይማኖት የሚገለጸው ትህትናን በማስቀደም በቃል፣ በፍቅርና በተግባር ነው ።
"ምዕመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምሮ በመመራት በፍቅርና በጋራ አብሮ መኖርን በማጠንከር ለእውነት መቆም ያስፈልጋል" ብለዋል።
ሃይማኖተኛ ጥላቻን በማንገስና እራስን በመኮፈስ እንደማይገለፅ ጠቅሰው ትህትናን፣ ፍቅርን፣ አንድነትንና መተባበርን ማጠንከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የከተራና የጥምቀት በዓልን በመተባበርና በመተሳሰብ እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ማሳለፍ እንደሚገባ ብፅዑ አቡነ አብረሀም አስገንዝበዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው "በበኩላቸው የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ህዝቡ ጥቃቅን ልዩነቶችን በማሰወገድ ለጋራ ህልውና በአንድ ላይ የቆመበት ወቅት ላይ ሆኖ የሚከበር በመሆኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው በብዙ መንገድ ልዩ ያደረገዋል" ብለዋል።
ወጣቱ በዓሉ በሰላም እንደተጀመረ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ አካላት ጋር እያደረገ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በተመሳሳይ የከተራ በዓል በጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብር ማርቆስ፣ ሰቆጣ፣ መተማና ሌሎች ከተሞች ታቦታቱ በሰላም ወደ ማደሪያቸው አርፈው፤ በሰላም ተጠናቋል።