በሀዋሳ የጥምቀት በዓል ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ የጥምቀት በዓል ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል
ሀዋሳ፤ ጥር 10/2014 (ኢዜአ)፡ በሀዋሳ ከተማ የጥምቀት በዓል ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ።
የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረሰ ቡሳሮ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጥምቀት በዓል በሀዋሳ ከተማ በድምቀት ከሚከበሩ ህዝባዊና ሐይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
በዓሉ ከከተራ ጀምሮ እስከፍፃሜው ድረስ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የከተማዋ ፖሊስ ከክልሉ ልዩ ኃይልና ከፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና ሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል ።
የሠላምና ፀጥታ ሥራ ያለ ህብረተሰብ ተሳትፎ ስኬታማ እንደማይሆን የጠቆሙት ኃላፊው፤ እስከ መንደር ድረስ ባሉ መዋቅሮች ህዝቡን የማስገንዘብና የግንኙነት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የጥምቀት በዓል የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።
ዳያስፖራውም ሆነ ወደ ከተማዋ መጥተው ጥምቀትን የሚያከብሩ እንግዶች በሠላም ወጥተው እንዲገቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጸጥታ ማስከበር ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የከተማዋ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በክብረ በዓሉ ላይ ከሚያደርገው እጀባ ባሻገር ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ አፋጣኝ ፍትህ መስጠት እንዲቻል ከጥምቀተ ባህሩ አቅራቢያ ዳኛ ፣ ዐቃቤ ሕግና መርማሪ ፖሊስ የተሟላለት ጊዜያዊ ችሎት መቋቋሙን ገልጸዋል ።
ህብረተሰቡ ማንኛውንም የወንጀል ድርጊት ሲመለከት 0462201046 ወይም 0912030089 በመደወል ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት እንደሚችልም አስታውቀዋል ።
ከዚህ በፊት በከተማዋ ይስተዋሉ የነበሩ የንጥቂያና ዝርፊያ ወንጀሎች በአብዛኛው ይፈፀሙ የነበሩት ሰሌዳ በሌላቸው ባለሁለት እግር ሞተር ተሽከርካሪዎች እንደሆነ ጠቅሰዋል ።
ይህን ለመከላከል በተደረገው የቁጥጥር ሥራ በርካታ ሰሌዳ አልባ ሞተሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸው፤ ይህ ተግባርም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ላዕከ ወንጌል ቀሲስ ደግፌ ባንቡራ፤ የጥምቀት በዓል ዐበይት ከሆኑ የቤተክርቲያኒቱ የአደባባይ በዓላት መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚገለፅበት መሆኑን አመልክተዋል።፡
በዓሉ የዕምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የሌላ ዕምነት ተከታዮችም የሚታደሙበት ፤ ኢትዮጵያዊነት ደምቆ የሚታይበትም እንደሆነ አስረድተዋል።
በዓሉ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ እሴቱን እንደጠበቀ በሠላም እንዲከበር ቤተክርስቲያኗ የሃይማኖት አባቶች ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና የተለያዩ ማህበራትን ያሳተፉ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ዝግጅት ማድረጓን ተናግረዋል ፡፡
ከከተማ አስተዳደሩ ከፖሊስና አመራር አካላት ጋርም እንዲሁ የጋራ ዕቅድ አውጥተን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል ፡፡
ጥምቀት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ፣የሳይንስና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ / ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱ መሆኑን ይታወቃል።