ባለሥልጣኑ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርጥ ዘርና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ባለሥልጣኑ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርጥ ዘርና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ባህር ዳር ፣ ጥር 10/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርጥ ዘርና የህክምና ቁሳቁስ ለአማራ ክልል ግብርናና ጤና ቢሮዎች ድጋፍ አደረገ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በድጋፍ ርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት ባለሥልጣኑ በሥሩ የሚገኙ ድርጅቶችን በማስተባበር ድጋፉን አድርጓል።
ባለሥልጣኑ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ያጋጠመውን አገራዊ ችግር ለመፍታት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የጥረቱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፉ 4 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 695 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና 170 ዊልቸሮችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።
'ክልሉ መልሶ እስኪቋቋም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት መጠነ ሰፊ ጉዳት ካደረሰባቸው ዘርፎች ግብርና አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ቡድኑ በፈፀመው ወረራ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ዘር ሳይሸፈንና የደረሰ ሰብልም ሳይሰበሰብ ቀርቷል፤ በዚህም ከ40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ታጥቷል" ብለዋል።
ምርጥ ዘሩን በሰሜን ወሎ ዞን ለሚገኙ አርሶ አደሮች በማከፋፈል በበልግና በመስኖ ወቅቶች የታጣውን ምርት ለማካካስ እንደሚውል ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው ባለሥልጣኑ ያደረገው የመድሀኒትና የዊልቸር ድጋፉ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የጤና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ሌሎች ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ የቢሮ ሀላፊው ጠይቀዋል።