ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ 'ደም እና ቲሹ' ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት ለመሰብስብ ካቀደው የደም መጠን ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ አሳክቷል

ጥር 10/2024/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ 'ደም እና ቲሹ' ባንክ ባለፋት ስድስት ወራት ለመሰብሰብ ካቀደው የደም መጠን ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ 'ደምና ቲሹ' ባንክ የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን አበጀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ  በበጎ ፈቃድ ደም የመለገስ ባህል እያደገ መጥቷል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ባንኩ ለመሰብሰብ ካቀደው የደም መጠን ውስጥ  ከ95 በመቶ በላይ ማሳካቱን ተናግረዋል።

በዚህም 188 ሺህ 900 ከረጢት ደም መሰብስብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በአሸባሪው የህወሃት ወረራ ምክንያት ከስራ ውጪ የሆኑ አራት የደምና ቲሹ ባንኮች ወደ ስራ እንደሚገቡ ጠቅሰው፤ በዚህም በቀጣይ የባንኩን አፈጻጸም የበለጠ ከፍ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ኀብረተሰቡ 'ደሜን ለመከላከያ ሰራዊት' በሚል ሀሳብ በስፋት የደም ልገሳ መርሃ-ግብሮችን ሲያካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በበጎ ፈቃደኝነት የሚደረገው የደም ልገሳ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያግዙ ቅስቀሳዎች በተጠናከረ መልኩ መከናወናቸውንም  አንስተዋል፡፡

በዚህም በአዲስ አበባ ያሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ደም እንዲለግሱ ማድረግና ሌሎች አደረጃጀቶችም በዚህ ተግባር እንዲሳተፉ በማድረግ የመደበኛው ደም ለጋሽ ቁጥር እንዲጨምር ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በዓመቱ 390 ሺህ ከረጢት ደም ለመሰብስብ እቅድ መያዙን ገልጸው፤ ባንኩ ይህን ለማሳካት ከትምህርት ቤት ማህበረሰብና ከወጣቶች ጋር በጋራ ይሰራል ነው ያሉት።

ኀብረተሰቡ ደም መስጠት ህይወት ማዳን መሆኑን በመገንዘብ በየሶስት ወሩ ደም የመስጠት ባህሉን እንዲያጎለብት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም