የበዓሉ በሰላም መከበር የቱሪዝም እንቅስቃሴን በማነቃቃት ዘርፉ እያደገ እንዲመጣ ያስችላል

77

ጎንደር ፤ ጥር 10/2014(ኢዜአ) የጥምቀት በዓል በሰላም መከበር የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማነቃቃት በተሻለ ደረጃ እያደገ እንዲመጣ የሚያስችል መሆኑን የአማራ ከልል ርዕሰ መሰተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የከተራና የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በጎንደር ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤  በዓሉን በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ተገኝቶ ማክበር ለየት ያደርገዋል።

"በተለይም ክልሉ ባለፉት ወራት በወረራና ጦርነት ውስጥ ከመቆየቱ አንፃር በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ማክበር መቻሉ አሁን የክልሉን የሰላምና የደህንነት ሁኔታ የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

የበዓሉ በሰላም መከበር የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲነቃቃና በተሻለ ደረጃ እያደገ እንዲመጣ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች መበራከት በጎንደር ታሪክ በአንድ ቀን ከ20 በላይ የአውሮፕላን በረራ በማካሄድ ሪከርድ መስበር መቻሉንም ዶክተር ይልቃል ገልጸዋል።

ወደ ጎንደር የሚመጡ እንግዶች በበዓሉ ከመታደም ባሻገር በከተማዋ ውስጥና አካባቢው የሚገኙ ቅርሶችን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል።

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዛሬ በራስ ግንብ ሙዚየም የተዘጋጀው የጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች አውደ ርዕይ  ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም