በሕልውና ዘመቻው የተገኘውን ድል ዘላቂነት ለማረጋገጥ በህብረትና በአንድነት መስራት ይገባል

ጎንደር፣ ጥር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሕልውና ዘመቻው የተገኘውን ድል ዘላቂነት ለማረጋገጥ በህብረትና በአንድነት መስራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍለ አስገነዘቡ፡፡

ለፀጥታ መዋቀሩ የተዘጋጀ የምስጋና የንጉስ እራት ግብዣ በዓፄ ፋሲል ቤተ-መንግሥት ዛሬ ምሽት ላይ ተከናውኗል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ የአማራን ሕልውና ለማስከበርና የኢትዮጵያን አንድነት አጽንቶ ለማስቀጠል ረጅም ርቀት ለሚጠይቀው ትግል መዘጋጀት ይግባል።

ለአማራ ሕልውና ፀር የሆነውና የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስ የተነሳው አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ዳግም እኩይ ድርጊቱን ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

"ሕዝባችን ለዳግም ጥቃትና ወረራ እንዳይጋለጥ ዝግጅታችን የማይቋረጥ መሆን አለበት" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሕልውና ዘመቻው አስተዋጽኦ ላደረገው የፀጥታ መዋቅርና ለሕዝቡ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው የከተማው ሕዝብ ለሕልውና ዘመቻ መሳካት ልጆቹን መርቆ ከመሸኘት ጀምሮ ስንቅ አዘጋጅቶ ወደ ግንባር በመላክ አስታዋጽኦ እንደነበረው አስታውሰዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም