ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበር ጋር በመተባበር ያሳደሳቸውን የ12 የአቅመ ደካማ ቤቶች ለነዋሪዎች አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበር ጋር በመተባበር ያሳደሳቸውን የ12 የአቅመ ደካማ ቤቶች ለነዋሪዎች አስረከበ
ጥር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበር ጋር በመተባበር እድሳት ያደረገላቸውን የ12 የአቅመ ደካማ ቤቶች ለነዋሪዎች አስረከበ፡፡
ቤቶቹን ለማደስ አራት ወራትን የፈጀ ሲሆን ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የከተማ ልማትና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ፤ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በዚህን ወቅት የቤቶቹ እድሳት በመደጋገፍ የአካባቢንና መቀየርና አገር ማልማት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።
እርስ በእርስ በመከባበርና በመዋደድ ጥላቻና መገፋፋትን ማስቀረት ይገባል ነው ያሉት።
በእድሳቱ ለተሳተፉ ተቋራጮችና ባለሃብቶች ምስጋና አቅርበው፤ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎችን ለመመከት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ በጋራ መሳተፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ አቅመ ደካማ ዜጎችን ለማገዝ በሚያስችሉ በጎ ተግባራት ላይ ለሚሳተፉ አካላት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግርማ ሃብተማርያም በበኩላቸው
ማህበሩ አባላቱን በማስተባባር የበጎ አድራጎት ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ለህልውና ዘመቻው የገንዝብና የአይነት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።
ማህበሩ አባላቶቹን በማስተባበር የአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳት ላይ መሳተፉን ጠቅሰው፤ ይህ ዜጎችን የመደገፍና የመርዳት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የቤት እድሳቱ ተጠቃሚ ከሆኑ መካካል አቶ ወንደስን ምትኩ እና ወይዘሮ ቀለሟ ማሞ የኖሩበት የነበረው ቤት ዝናብንና ብርድን መከላከል እንኳ የማይችል እንደነበር አስታውሰው፤ የቤት አድሳቱ የዘመናት ችግራቸውን እንደቀረፈላቸው ተናግረዋል፡፡
በቤት እድሳቱ ለተሳተፉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡