ዳያስፖራዎች እየተዝናኑ የኢትዮጵያን ቱባ ባህሎች የሚያውቁበት ዝግጅት ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራዎች እየተዝናኑ የኢትዮጵያን ቱባ ባህሎች የሚያውቁበት ዝግጅት ሊካሄድ ነው
ጥር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራዎች እየተዝናኑ የኢትዮጵያን ቱባ ባህሎች የሚያውቁበት ዝግጅት ከጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት እንደሚካሄድ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው እንደገለጹት፤ መርሃ-ግብሩን ያዘጋጁት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር እና "ኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንት" የተሰኘ ድርጅት በጋራ በመሆን ነው።
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ በበኩላቸው ጥር 22 ቀን 2014 ዓ.ም አምስት ሚሊዮን ሰዎች ይታደሙታል ተብሎ የሚጠበቅና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወን የ"ቡና ጠጡ" መርሃ_ግብር እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይን ጨምሮ በክልል የሚገኙ የማህበሩ የቅርንጫፍ ቢሮዎች በኩል የሚከናወን መሆኑንም ገልጸዋል።
ዓላማውም ኢትዮጵያ ከቡና ጋር ያላትን ቁርኝት በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ለማስተዋቅ መሆኑን አስታውሰው፤ "ቡና ጠጡ" ዝግጅቱ በነጻ የሚደረግ እንደሆነ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ እለት መነሻውን አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ያደረገ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር እና የምሽት የሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚኖር የተናገሩት ደግሞ ኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንት ዋና ስራ አስኪያጅ ሞቲ ሞረዳ ናቸው።
ከዳያስፖራዎች በተጨማሪ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በመርሃ ግብሩ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼