ቀጥታ፡

ወልድያ ዩኒቨርስቲን ስራ ለማስጀመር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ደሴ፣ ጥር 9/2014 (ኢዜአ) የተለያዪ ዩኒቨርሲቲዎች በአሽባሪው ህወሀት ውድመት የደረሰበትን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ስራ ለማስጀመር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን ያደረጉት ጂንካ፣ዲላ፣ ወላይታና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉዲሼ እንደገለፁት አሸባሪው የህወሀት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፈተው ጦርነት ያደረሰውን ሁለተናዊ ጉዳትና ጫና በጋራ መመከት ያስፈልጋል ።

ዩኒቨርሲቲው በአሸባሪው ወራሪ ሀይል የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በሚችለው አቅም እንደሚደግፍ ተናግረዋል ።

ወልድያ ዩኒቨርሲቲን ስራ ለማስጀመር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ በዩኒቨርሲቲያቸው ከተወሰነው የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ውስጥ በዛሬው እለት 3 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ለተማሪዎች ክሊኒክ፣ መመገቢያ፣ መማሪያና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጋቸውን አመልክተዋል ።

የወላይታ ዩኒቨርስቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብርሃም ቦሻ በበኩላቸው "ዩኒቨርሲቲውን በሁለት ወር ውስጥ ስራ ለማስጀመር የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል።

ዩኒቨርስቲውን ስራ ለማስጀመር የሚያደረገውን ጥረት ለመደገፍ ዛሬ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው  የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ድጋፉ ኮምፒውተር ፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ የጽህፈት መሳሪያዎችን ጨምሮ የህክምናና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው  27 ዓይነት ቁሳቁሶችን ድጋፍ መደረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርስቲ ተወካይ አቶ ይመኑ ዳካ ናቸው።

በዩኒቨርሲቲው ፍላጎት መሰረት የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር የሚያግዙ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

"ተጨማሪ ድጋፍ በማድረግ ዩኒቨርስቲውን በጋራ በቅርቡ ስራ እናስጀምራለን "ብለዋል።

ቀሪውን የቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገው ደግሞ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ነው።

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አበበ ግርማ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ ዩኒቨርሲቲውን  መሉ በሙሉ ማውደሙን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲውን መልሶ በማቋቋምና በመጠገን በሁለት ወር ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ዘጠኝ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበው አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በመጭው የካቲት 2014 ዓም ተመራቂና አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል ።

በዛሬው እለት  አራት ዩኒቨርሲቲዎች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው  ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው  "የተደረገው ድጋፍ ትምህርት ለመጀመር በቅድሚያ የሚያስፈልጉ  ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑ እቅዳችንን ለማሳካት አቅም ይሆነናል" ብለዋል ።

ፕሬዝዳንቱ ለተደረገው ወድጋፍ አመስግነው የኢትዮጵያ ህዝብና ተቋማት እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስተምር እንደነበር በስነ ስርአቱ ላይ ተመላክቷል  ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም