ዳያስፖራው የአገሩን ምርት በመግዛትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ሚናውን መወጣት አለበት

43

ጥር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው የአገሩን ምርት በመግዛትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የስራ፣ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ጥሪ አቀረቡ።

''የኢትዮጵያን ይግዙ'' በሚል መሪ ሀሳብ የአገር ውስጥ ምርቶችን ለዳያስፖራው የሚያስተዋወቅ ኤግዚቢሽንና ባዛር  ዛሬ በአዲስ አበባ መቻሬ ሜዳ በይፋ ተከፍቷል።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከ150 በላይ የአገር ውስጥ አምራች ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ለገበያ ከቀረቡት የአገር ውስጥ ምርትና አገልግሎቶች መካከል የቆዳ ውጤቶች፣ የአገር ባህል አልባሳት፣ የግብርና ውጤቶች፣ የባልትና ውጤቶችና ሌሎች ምርቶች ይገኙበታል።

ኤግዚቢሽንና ባዛሩን በይፋ የከፈቱት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ  ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ዳያስፖራው የአገሩን ምርት በመግዛትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአዲስ አበባ የስራ፣ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ የኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ በበኩላቸው ከታህሳስ 20 ጀምሮ በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች በተደረገው ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ኤግዚቢሽንና ባዛሮቹ ላይ የኢትዮጵያዊያን ውብ የፈጠራ ውጤቶች መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የአምራች ኢንተርፕራይዞችን በማበረታታት ኢኮኖሚውን በዘላቂነት ለመገንባት ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከጥር 9 እስከ 16 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል፡፡

በመዲናዋ ከታህሳስ 20 ጀምሮ አምስት የተለያዩ የኤግዚቢሽንና ባዛሮች መዘጋጀታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በመቻሬ ሜዳ ዛሬ በይፋ የተከፈተው ለ6ኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም