ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማጎልበት ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የአሰራር ከፍተቶችን ለመፍታት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማጎልበት ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የአሰራር ከፍተቶችን ለመፍታት ይሰራል
ጥር 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማጎልበት በከተሞች አካባቢ ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የአሰራር ከፍተቶችን ለመፍታት እንደሚሰራ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ያበለጸገውን የቤቶች መረጃ አስተዳደር ሶፍት ዌር ዛሬ በይፋ ወደ ስራ አስገብቷል፡፡
ስፍትዌሩ በአዲስ አበበ ከተማ ስራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ በቀጣይ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በዚህን ወቅት በከተሞች ካለው የመኖሪያ ቤት እጥረት ባሻገር በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ መረጃ አለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡
መንግስት በከተሞች አካባቢ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከመንግስት በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ሚኒስቴሩ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማጎልበት ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የአሰራር ክፍተቶችን ለመፍታት እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት፡፡
ከዚህ አኳያ በዛሬው እለት በይፋ ወደ ስራ የገባው የቤቶች መረጃ አስተዳደር ሶፍት ዌር መረጃዎችን ለመሰብሰብ ፤ለማደራጀት እና ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ቀልጣፋ፤ ቀላልና ግልፅ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት በገባው ቃል መሰረት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለት በመዲናዋ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው ሶፍት ዌር በዚህ ረገድ በአብነት አንስተዋል፡፡
ሶፍት ዌሩን ተግባራዊ በማድረግ ኀብረተሰቡ ቀልጣፋና ግልጽ አገልግሎት እንዲያገኝ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት አለመኖሩ ዘርፉን ለብልሹ አሰራር አጋልጦት መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ያስሚን ዋቢረቢ ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ ተግባራዊ የተደረገው ሶፍት ዌር ችግሩን በመቅረፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን ጨምሮ ከ150 ሺህ በላይ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች መኖራቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡