ባህላዊ የሽምግልና ስርዓቶችን ለእርቅና ብሔራዊ መግባባት ጥቅም ላይ በማዋል የህዝቦችን አብሮነት ማጎልበት ይገባል

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2014( ኢዜአ) በኀብረተሰቡ ዘንድ ያሉ ባህላዊ የሽምግልና ስርዓቶችን ለእርቅና ብሔራዊ መግባባት ጥቅም ላይ በማዋል የህዝቦችን አብሮነት ማጎልበት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡

አቶ አበራ በቀለ የመስቃን ቤተ ጉራጌ የባህል ሽማግሌ ሰብሳቢ ሲሆኑ ለረጅም ዓመታት በሽምግልና ቆይተዋል።   

በጉራጌ ባህል ሰላምን ፍቅርና አንድነት ለማስፈን የሚያግዙ ቱባ ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።        

በመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት እንዲቋጭ ያደረገው ባህላዊ ሽምግልና እና  የእርቅ ሥነ ስርዓት መሆኑን ጠቁመው፤ ባህላዊ ሽምግልና ለሰላምና አንድነት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡    

በቤተ ጉራጌ  "ማጋ"፣ "ፈረዛገኝን" የተሰኙና ሌሎች ባህላዊ የሽምግልና እና እርቅ ስርዓቶች መኖራቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ያሉ ባህላዊ የሽምግልና እና እርቅ ስርዓቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

የሚፈጠሩ ልዩነቶች ወደ ግጭትና ደም መፋሰስ ከማምራታቸው በፊት በባህላዊ ሽምግልና በመፍታት የህዝቦችን አብሮነት ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሌላው የአገር ሽማግሌ አቶ አያሌው ታደሰ በበኩላቸው የአገር ሽማግሌዎች ለሰላም መስፈን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡

የአገር ሽማግሌዎች ባህላዊ እርቅን በመጠቀም በኀብረተሰቡ ዘንድ ተከስተው የነበሩ አለመግባባቶችንና የሰላም እጦትን መፍታት እንደቻሉም ነው የገለጹት፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ችግሮች በባህላዊ እርቅ የተፈቱት ህዝቡ የአገር ሽማግሌዎችን በመስማቱ ነው ያሉት አቶ አያሌው ታደሰ፤ ከዚህ አኳያ የአሁኑ ትውልድ አባቶችን መስማት እንዳለበት መክረዋል፡፡     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም