አፍሪካ በውጭ የሚኖሩ ተወላጆችና ዜጎቿን ጉዳይ የሚያስተባብር ተቋም ሊኖራት ይገባል

135

ጥር 8/2014 /ኢዜአ/አፍሪካ በውጭ የሚኖሩ ተወላጆችና ዜጎቿን ጉዳይ የሚያስተባብር ተቋም ሊኖራት እንደሚገባ በደቡብ አፍሪካ ስዌኔ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰርና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ ገለጹ።

የአፍሪካ መንግስታት የአፍሪካን ዳያስፖራ ከአህጉሪቷ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ጋር የማስተሳሳር ስራ ማከናወን ይኖርባቸውልም ነው ያሉት።

አፍሪካውያን በተለያዩ አጋጣሚዎች ማለትም ለትምህርት፣ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር ሲሉ ይሰደዳሉ።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን “የአፍሪካ ተወላጅ ሆነው ከአህጉሪቷ ውጭ የሚኖሩ የአፍሪካን ግንባታና ልማት ለመደገፍ ፍላጎት ያላቸውን አፍሪካውያንና ትውልደ አፍሪካውያንን” የአፍሪካ ዳያስፖራ ብሎ ሰይሟቸዋል።

የአፍሪካ ዳያስፖራ ካለው አቅም አኳያ አንዳንዶች “የአፍሪካ ሚስጥራዊ መሳሪያ” በማለት ይጠሩታል።

በደቡብ አፍሪካ ስዌኔ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰርና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ የአፍሪካ ዳያስፖራ አፍሪካዊ ማንነትን መላበስ አለበት ይላሉ።

ዳያስፖራው ታሪክና ባህሉ የሚያንጸባርቅ ከሆነ እርስ በእርሱ እየተሳሰረና አንድ እየሆነ መምጣት እንደሚችልም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድም “ኢትዮጵያ የራሷ የዳያስፖራ ተቋም እንዳላት ሁሉ አፍሪካም የዳያስፖራ ጉዳዮችን የሚያስተባብርና የሚመራ የአፍሪካ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያስፈልጋታል ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት እ.አ.አ በ2021 ሰሜን፣ምዕራብ፣ደቡብ፣ሰሜንና ማዕከላዊ ብላው ከሰየማቸው ቀጠናዎች በተጨማሪ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ዳያስፖራዎችን እንደ “ስድስተኛ ቀጠና” አድርጎ መሰየሙ መልካም የሚባል እመርታ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁንና ይህ “ስድስተኛ ቀጠና” በአፍሪካ ካሉት ሌሎች አምስት ቀጠናዎች ጋር በሚፈለገው መልኩ አለመተሳሰራቸውን ነው ፕሮፌሰር ሙላቱ ያስረዱት።

ስለሆነም የአፍሪካ ሕብረትና አባል አገራቱ የአፍሪካውን ዳያስፖራ ከአፍሪካ ጉዳዮችና የኢኮኖሚ መስክ ጋር የማስተሳሰር ስራ ሊያከናውኑ ይገባል ብለዋል።

በተለይም ሕብረቱ በዓመታዊ ስብስባው የዳያስፖራውን ጉዳይ እንደ አንድ የመወያያ አጀንዳ አድርጎ ሊያቀርበው ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ የአፍሪካ ዳያስፖራ ተወካዮች ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ አፍሪካን በመገንባት ውስጥ ያላቸውን ራዕይ በሀሳብ እንዲያቀርቡ በማድረግ ከአህጉሪቷ ጋር ያላቸውን ትስስር ማጎልበት እንደሚቻልም አመልክተዋል።

ትስስሩን በማጠናከርም የአፍሪካ ዳያስፖራ ለአፍሪካ አህጉር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ መጨመርና ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚቻልም ነው ፕሮፌሰር ሙላቱ የገለጹት።

እ.አ.አ በ2021 በውጭ አገራት የሚገኙ የአፍሪካ ዳያስፖራዎች 41 ቢሊዮን ዶላር ወደ አፍሪካ  መላካቻውንና እ.አ.አ በ2020 ከነበረው አንጻር በሶስት ቢሊዮን ዶላር ቀንሷል፤ የቀነሰበት ምክንያት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በፈጠረው ጫና መሆኑን  የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም