በአሸባሪው ህወሀት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትን ከቀድሞ ይዞታቸው በተሻለ ለመገንባት እንሰራለን -ዳያስፖራዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአሸባሪው ህወሀት ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትን ከቀድሞ ይዞታቸው በተሻለ ለመገንባት እንሰራለን -ዳያስፖራዎች
ባህር ዳር ጥር 08/2014-(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ሀይል ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትን ከቀድሞ ይዞታቸው በተሻለ መልሶ ለመገንባት የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ዲያስፖራዎች አስታወቁ ።
ክልል አቀፍ የዳያስፖራ ትብብር ሲምፖዚየምና የእራት ግብዣ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
ከአሜሪካን አገር ቨርጅኒያ ግዛት የመጡት አቶ ሲሳይ ደማሙ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ለአዕምሮ የሚከብድ ግፍ ፈጽሟል።
አሸባሪ ቡድኑ ይህን እኩይ ድርጊት የፈጸመው የኢትዮጵያ ህዝብ የፍቅርና የመተሳሰብ እሴትን በመበጣጠስ አገር ለማፍረስ ካለው ዓላማ የመነጨ መሆኑን አመልክተዋል።
በወራሪው ቡድን የተፈጸመውን ውድመት በመገንዘብ በግላቸው ካዋጡት ግማሽ ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ጓደኞቻቸውን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በማስተባበር 12 ሺህ ዶላር በመሰብሰብ ለሰብአዊ ድጋፉ ማዋላቸውን ገልጸዋል።
አሸባሪው ቡድኑ ያደረሰው ውድመትና የፈጸመው ዝርፊያ ያስቆጫቸው መሆኑን ጠቁመው "ያለንን አቅም በማስተባበር የወደሙ ተቋማትን ከቀድሞ ይዘታቸው በተሻለ በመገንባት ለአገልግሎት ለማብቃትና አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንሰራለን" ብለዋል።
ከአሜሪካን ችጋጎ የመጣው የማህበረሰብ አንቂ አቶ ዳንኤል ተሰማ በበኩሉ፣ በከፈተው ዩቱዩብ ቻናል አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን ኢትዮጵያን አስመልክተው ያስተላለፉትን ሃሰተኛ ዘገባ በማጋለጥ ሲሞግት መቆየትን አስታውሷል።
ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን አሸባሪው ቡድን እያደረሰ ያለውን ጥፋት በአሜሪካን ለመንግስት ተቋማትና ድርጅቶች በአደባባይ በማጋለጣቸው በዲፕሎማሲው መስክ ለውጥ እየታየ መሆኑን ጠቅሷል።
በውጭ አገር ለ25 ዓመታት እንደቆየ የገለጸው አቶ ዳንኤል "አሸባሪው ህወሓት በወረራቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ብገምትም ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ ያየሁት ግን ሰው ሆኜ መፈጠሬን እንድጠላ አድርጎኛል" ብሏል፡፡
በወረራ ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች በሽብር ቡድኑ የተፈጸመው የሰብአዊና ቁሳዊ ሃብት ለማመን የሚያዳግት መሆኑን ተናግረዋል።
የማህበረሰብ አንቂው እንዳለው ከኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ በመልሶ ግንባታውና በዲፕሎማሲ መስክ የሚያደርጉትን ትግል ከማጠናከር ባለፈ ዲያስፖራው ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ የቅስቀሳ ስራ እንደሚሰራ ተናግሯል።
ከኖርዌይ የመጡት ወይዘሮ ሰዋሰው ስለሺ በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሓት የተነሳበት አገር የማፍረስ ግብ ዳያስፖራው ከዳር ዳር አንዲነሳና ለዓለም ህዝብ በአንድነት እንዲጮህ አድርጎታል" ብለዋል።
"በዲያስፖራ ታሪክ ውስጥ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ ያለው በአንድነት በመቆምና መደበኛ ስራውን ጭምር በመተው ለአገሩ የሞገተበት ጊዜ እንዳሁኑ ታይቶ አይታወቅም " ሲሉም ተናግረዋል።
እስካሁን በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ሲያደርጉ የነበረውን ድጋፍ በቀጣይም በመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራው በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
አንድ ዲያስፖራ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰበትን አንድ ቤተሰብ እንዲደግፍ የቀረበውን ሀሳብ በመደገፍ ሁለት ልጆችን ተረክበው በአገር ባህልና ወግ መሰረት እንደሚያሳድጉ አመልክተዋል።
ትናንት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደ ክልል አቀፍ የዲያስፖራ የትብብር ሲምፖዚየምና የእራት ግብዣ ለተቋማት መልሶ ግንባታና ለተፈናቀሉ ማቋቋሚያ ገንዘብ የማሰባሰብ መርሃ ግብር መካሄዱ ይታወቃል።