በመስቃንና ማረቆ ህዝቦች መካከል የተደረገው እርቅ ዘላቂ እንዲሆን የጥፋት ሃይሎችን በጋራ መታገል አለብን

ጥር 8/2014/ኢዜአ/ "በመስቃንና ማረቆ ህዝቦች መካከል የተደረገው እርቅ ዘላቂ እንዲሆን የጥፋት ሃይሎችን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ በጋራ መታገል አለብን" ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።

በጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን እና ማረቆ ወረዳ መካከል በጥፋት ሃይሎች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በባህላዊ መንገድ በእርቅ እንዲቋጭ ተደርጓል።         

ግጭቱ የተከሰተው ከሦስት ዓመት በፊት ሲሆን ከአከላለል ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ በጥፋት እና ጥቅም ፈላጊዎች ተባብሶ ሰፋ ወዳለ ግጭት አምርቶ ነበር።  

በግጭቱ ሳቢያ የሰዎች ህይወት ሲያልፍ የንብረት ውድመትና መፈናቀሎች ተከስተው ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ከሀያ ዘጠኝ ጊዜ በላይ እርቅ ለማምጣት ጥረት ቢደረግም ውጤት ሳይገኝ ቆይቷል።      

አሁን ላይ ግን ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎች አመራሩና ህዝቡ በጋራ በሰሩት ስራ ችግሩ በውይይት ተፈቶ በእርቅ ተቋጭቷል።

         

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ኢንሴኖ የሠላም ጉባኤ ተካሂዷል።   

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት ያለፈውን የመከራ ጊዜ በእርቅና በይቅርታ ከመሻገር በላይ የሚክስና የሚፈውስ ነገር የለም፤ ሁለቱም ወገኖች ይቅር ተባብለው የቀደመውን አብሮነት በማጽናታቸው ምስጋና እና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።  

"ያለፈው ነገር ቁጭት የሚፈጥር ቢሆንም ለቀጣዩ ግን ትምህርት የሚሆን ነው" ያሉት አቶ ርስቱ አሁን የተፈጠረው እርቅ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጥር የጥፋት ሃይሎችን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ነው ያሉት።

የግጭቱ ዋነኛ ምክንያት አሸባሪው ህወሃት ከእኩይ ዓላማ አስፈጻሚዎች ጋር በመተባበር ሁለቱን ህዝቦች ለመለያየት የሸረበው ሴራ መሆኑን ጠቁመው አጥፊዎችና በመታገል አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።   

ከዚህ በኋላ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም በመፍጠር የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ማቋቋምና ልማትን ማስቀጠል ይሆናል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሃመድ ጀማል፤ አሁን የተገኘው ሰላም በአስተማማኝ መሰረት ላይ የሚቆመው ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ግጭት የሚያነሳሱ አካላትን በጋራ መፋለም ሲችሉ ነው ብለዋል።     

የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዴ በበኩላቸው በሁለቱ ህዝቦች መከካል እርቅ የወረደበት መንገድ ሌሎች ችግሮችንም መፍታት እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል።  

የአገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ ባልቻ ገለቶ፤ በሽምግልና ሂደቱ ሁሉንም ማህበረሰብ የሚወክሉ የየአካባቢው ሽማግሌዎች መሳተፋቸውን አብራርዋል።        

የአገር ሽማግሌዎች አርቅ የማስፈን እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን መንግስት በሁሉም መስክ ያደረገው ድጋፍም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዕለቱም በሁለቱ ህዝቦች መካከል እርቅ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም