ቀጥታ፡

የጸጥታ ሃይሎች በቅንጅት የፈጸሙት ተጋድሎ ነጻነታችን እንድናስጠብቅ አስችሎናል

ባህርዳር፤ ጥር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች የአሸባሪውን ህወሓት ጥቃት ለመመከት የፈፀሙት ተጋድሎ ነጻነታችንና ክብራችን እንድናስጠብቅ አስችሎናል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

በባህርዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የዳያስፖራዎች የትብብር ሲምፖዚየም ማምሻውን ተጠናቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሲምፖዚየሙ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት ወረራ ፈጽሞባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሰብአዊ ጉዳት፣ ቁሳዊ ውድመትና ዝርፊያ ፈጽሟል።

በክልሉ ጥቃት ባደረሰባቸው አካባቢዎች የመንግስትና የግል ሃብት፣ የማህበራዊ ተቋማትንና ኢንዱስትሪዎችን ከማውደም ባሻገር በየደረሰበት ቦታ ሁሉ ግድያና አስገድዶ መድፈር በመፈጸም የእብሪተኝነት ጥጉን አሳይቷል ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ባካሄደው የተቀናጀ ትግል የአሸባሪውን ቡድን  ሽንፈት እንዳከናነበው ገልጸዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብና የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ባደረጉት ድጋፍና ትብብር አሁን ለተገኘው  ነጻነትና ክብር መብቃት መቻሉን ተናግረዋል።

"የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሀገራችን ላይ የደረሰውን የዲፕሎማሲ ጫና ለመቀልበስ ያደረጉት አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው" ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን ናቸው።

በዚህም አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራትና ድርጅቶች ይዘውት የነበረውን  አቋም እንዲያለዝቡ በማድረግ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል።

ዳያስፖራው በገንዘብ፣ በእውቀትና በክህሎት የህልውና ትግሉን በመደገፍ የደጀንነት ሚናውን በአግባቡ በመወጣቱ የክልሉ መንግስት አክብሮት አለው ብለዋል።

በቀጣይ በሚካሄደው የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ እንዲሁም ዘላቂ ኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ዳያስፖራው ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል የዳያስፖራ አስተባባሪ አቶ ሃብታሙ አዱኛ ዳያስፖራው በህልውና ዘመቻው የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

ዳያስፖራውን በአማራና በአፋር ክልሎች የደረሰውን ውድመትና ዘረፋ መልሶ ለመተካት በሚደረገው ጥረት፣ በኢንቨስትመንት ለማሳተፍና ለማደራጀት የተዘጋጀው ሲምፖዚየም የአጋዥነት ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።

ዳይስፖራውን ማህበረሰብ በማሳተፍ  ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገንዘብ ለማሰባሰብ ያለመ  የእራት ግብዣም ተካሂዷል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም