ከካሊፎርኒያና ከጀርመን የመጡ ዳያስፖራዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ከካሊፎርኒያና ከጀርመን የመጡ ዳያስፖራዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
ጥር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ከአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛትና ከጀርመን የመጡ ዲያስፖራዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።
የገንዘብ ድጋፉን ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሃሰን አስረክበዋል።
በካሊፎርኒያ ሳክራሜንቶ ከተማ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካይ አቶ አደም ለገሰ የተሰባሰበውን 247 ሺህ 670 ዶላር/12 ሚሊዮን 227 ሺህ 78 ብር/ አስረክበዋል።
የገንዘብ ድጋፉን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት ጦርነት በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን አንስተዋል።
በዚህ ውድመት በርካታ ዜጎች ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን ጠቁመው ድጋፉም እነዚህን ዜጎችን ለመደገፍና ለማቋቋም የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የገንዘብና ለተለያዩ ተቋማት የሚውል የአይነት ድጋፍ ለማድረግ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።
አቶ ትርፌ ፍቃዱ ደግሞ ከጀርመን ባቫሪያ ስቴት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ያሰባሰቡትን ከ1 ሚሊዮን 34 ሺህ ብር በላይ ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
በባቫሪያ ስቴት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቁጥር ከ1 ሺህ የማይበልጡ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘቡን በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህን መሰል ድጋፍ በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረው በተይም የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ሥራ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሃሰን በበኩላቸው ዳያስፖራዎቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ዳያስፖራዎቹ በቀጣይም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።