ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2014 ( ኢዜአ) ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ሆፕ ዎክስ የተሰኘ የህጻናት የዞረ እግር ሕክምና መስጫ ድርጅትና የአምድሁን ሪልስቴት ነዋሪዎችም እንዲሁ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
ድጋፉን ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሐሰን አስረክበዋል።
የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ በላቸው ዘውዴ ተቋማቸው ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ድጋፉ በፍትኃዊነት በአሸባሪው ቡድን ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖች እንዲከፋፈል በብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን በኩል እንዲያልፍ መደረጉንም አስረድተዋል።
አቶ በላቸው ተፈናቃዮቹ እስከሚቋቋሙ ድረስም ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ሆፕ ዎክስ የህጻናት የዞረ እግር ማከሚያ ድርጅትና የአምድሁን ሪልስቴት ነዋሪዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የሪልስቴቱ ነዋሪዎች ተወካይ አቶ ሰለሞን ተክለማርያም እንደገለጹት፤ ነዋሪዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት 200 ሺህ ብር የሚጠጋ ብር በማሰባሰብ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አድርገዋል።
የሆፕ ዎክስ ድርጅት ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው አበራ፤ መርዳትና መተጋገዝ አንደኛው የድርጅቱ መርህ መሆኑን ጠቁመው በችግር ላይ ለሚገኙት ወገኖች ድጋፍ በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሃሰን በበኩላቸው፤ የተደረገው ድጋፍ ወቅታዊና ለተፈናቃይ ዜጎች እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ችግር የኔም ችግር ነው የህዝቤ ችግር የእኔም ችግር ነው" በማለት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው ለዚህ በጎ ተግባራቸው ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ቀጣዩ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ከፍተኛ ሃብት የሚጠይቅ በመሆኑ መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።