ፌዴሬሽኑ የአገር ውስጥ ውድድሮችን የሚያዘምኑ ስራዎችን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴሬሽኑ የአገር ውስጥ ውድድሮችን የሚያዘምኑ ስራዎችን እያከናወነ ነው
ጥር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአገር ውስጥ የሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮችን ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ገለጸ።
25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ያለው ፌደሬሽኑ አትሌቲክሱን ውጤታማ ለማድረግ የረጅምና የአጭር ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን የፌደሬሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ተናግረዋል።
በእቅዱ መሰረት ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የስልጠና እና የውድድር አካሄድን ማዘመን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል።
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ስልጠና እና ውድድሮችን ለማዘመን አስፈላጊ የሆኑ ስራዎችን እየሰራ ነው ተብሏል።
በዚሁ መሰረት በተያዘው ዓመት በ9 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ ውድድሮችን ከመነሻ እስከ አጨራረስ ያለውን ውጤት በዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በመታገዝ የሚመዘግብ መሳሪያ ግዥ ተፈጽሟል።
ከዚህ ቀደም የውድድሩ አካሄድ በኤሌክትሮኒክስ ያልታገዘ በመሆኑ በአገር ውስጥ በሚካሄዱ ውድድሮች አትሌቶች የሚያስመዘግቡት ሠዓት በዓለም አትሌቲክስ ተቀባይነት አልነበረውም።
በመሆኑም የመሳሪያዎቹ መኖር በቀጣይ በአገር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች የሚመዘግቡ ሠዓቶች በዓለም አትሌቲክስ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው የተባለው።
እነዚህን መሳሪያዎች በዚህ ዓመት በሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወደ ተግባር ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ቢልልኝ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ የውጭ ምንዛሬ በመክፈል የሚኒማ ሠዓት ለማሟላት ከአገር ውጭ የሚያካሂዳቸውን ውድድሮች በአገር ውስጥ ማካሄድ የሚያስችሉ ተጨማሪ የአትሌቲክስ ውድድር መሳሪያዎች ግዥ እየተፈፀመ መሆኑንም አክለዋል።