አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰው ውድመትና ሰብአዊ ቀውስ ኢትዮጲያን የማፍረስ የረጅም ጊዜ እቅድ እንደነበረው ያሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰው ውድመትና ሰብአዊ ቀውስ ኢትዮጲያን የማፍረስ የረጅም ጊዜ እቅድ እንደነበረው ያሳያ ነው
ደሴ፤ ጥር 6/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ያደረሰው ውድመትና ሰብዓዊ ቀውስ ኢትዮጵያን የማፍረስ ለረጅም ጊዜ አቅዶ መስራቱን በግልጽ ያሳየ መሆኑ ተመለከተ፡፡
የእስልምና ጉዳይ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰበትን የወሎ ዩኒቨርሲቲን ተመልክተዋል፡፡
በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሱልጧን አማን እንደገለጹት፤ በሽብር ቡድኑ የወደሙትን ወሎና ወልድያ ዩኒቨርሲቲዎችን በቦታው በመገኘት ተመልክተዋል።
የሽብር ቡድኑ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን እንዳልሆኑ አድርጎ መዝረፉና ማውደሙ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለረጅም ጊዜ አቅዶ መስራቱን አረጋግጧል ብለዋል፡፡
ተዘዋውረው የተመለከቱት ውድመትም ለማመን የሚከብድ፣ ዘግናኝ፣ ከሰው ልጅ ያውም ከወገን የማይጠበቅ አሳፋሪ የታሪክ ጠባሳ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ድርጊቱ እንዳይፈጸም ቀድመን የሐይማት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም በጋራ ጥረት ብናደርግም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ሰላም ማረጋገጥ ባለመቻሉ ሳይሳካ ቀርቷል ሲሉ አስታውሰዋል።
ሆኖም ቡድን በጭካኔ ወገኑን ይወጋል፤ ያወድማል ብለን አላሰብንም ነበር ብለዋል።
የተመለከትነውን ሁለተናዊ ጥፋት ለህብረተሰቡና ለአጋር አካላት በማሳየትና በማስረዳት ድጋፍ ለማድረግና በዘላቂነት ለማቋቋም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ አብራርተዋል።
ውድመቱ ከፍተኛ በመሆኑ በመንግስት ብቻ ማቋቋም ስለማይቻል የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኦሮሚያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ሁለተናዊ ጉዳት በወሬ ብንሰማም በዓይናችን ተመልክተን ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በስፍራው ተገኝተናል ብለዋል።
ትውልድ የሚቀረጽበትን የትምህርትና ሰብዓዊ አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ተቋማትን ጨምሮ መልሰው ጥቅም እንዳይሰጡ አድርጎ ማውደሙን በአካል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡን አስተባብረንም የወደመውን ገንብተን አገልግሎት እንዲሰጥ እናደርጋለን፤ ከመንግስት ጎን ተሰልፈን የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግም ዝግጁ ነን ብለዋል ሸህ ኢብራሂም፡፡
የዓለም አቀፍ ታሪክ ጥናትና ምርምር ባለሙያ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጠላቶቻችን ቢሰሩም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ እያከሸፈው ነው ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር አደም ፤በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መፋጠን ያንገበገባቸው ጠላቶቻችንን በጋራ መክተን የአብሮነትና የነጻነት ታሪካችን ማስቀጠል ከሁላችንም ይጠበቃል ነው ያሉት ፡፡
የሽብር ቡድኑ ያደረሰው ውድመትም በታሪክ ሰንዶ በመያዝ ትውልዱ እንዲማርበትና የሽብር ቡድኑ ሲያፍር እንዲኖር መደረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ አቶ አፍወርቅ አዳነ ፤ አሸባሪው ህወሓት ዩኒቨርሲቲውን ሙሉ በሙሉ መዘርፉንና ያልቻለውንም ማውደሙን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ተቋማትንና ህብረተሰቡን በማስተባበር የወደመውን በመጠገንና በመተካት መማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡