በዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣት የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣት የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ ነው
ጥር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዳያስፖራውን ወደ አገር ቤት መምጣት ተከትሎ ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ 'ጥምቀትን በጎንደር' የተሰኘው የዳያስፖራዎች መርሃ-ግብር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ወደ አገር ቤት ለገቡ ዳያስፖራዎችን ለማስተናገድ የተዘጋጁ አገራዊ ሁነቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት ክብረ በዓል የፊታችን ጥር 11 ቀን በድምቀት እንደሚከበር ገልፀዋል።
ዳያስፖራዎቹ በቆይታቸው ከሚሳተፉባቸው አገራዊ መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ የሆነው የ'ጥምቀትን በጎንደር' መርሃ ግብር ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል ነው ያሉት፡፡
ከጥምቀት ክብረ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞም በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ የኢንቨስትመንት ምክክር መድረኮች፣ ዐውደ ርዕዮች፣ ባዛሮች፣ የኪነ-ጥበብ ምሽቶችና ሌሎች መድረኮች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።
የጥምቀት ክብረ በዓል አከባበር በጎንደር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸው፤ ዳያስፖራዎች እና የውጭ ቱሪስቶች በቀን እስከ 4 የአውሮፕላን በረራ ተዘጋጅቶ ከወዲሁ ወደ ጎንደር ከተማ እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ የጥምቀት መዳረሻ ቀናትም በቀን ከ11 በላይ በረራዎች እንደሚደረጉ ጠቅሰው፤ እንግዶች ይህን ዝግጅት እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህም በኮቪድ-19 እና ግጭት ምክንያት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ እንደሚያነቃቃ ተናግረዋል።
የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት መምጣት በተለይ ለቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት መልካም ዕድል ስለመፍጠሩም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የአገር ውስጥ ቱሪዝምን በማነቃቃት ታይቶ በማይጠገብ የኢትዮጵያ መስህቦች ላይ የጉብኝት ባህል እንዲዳብር ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼