በጋምቤላ ክልል የተፈጥሮ ደን ሀብትን ለመጠበቅ የደን አስተዳደር ፕላን ዝግጅት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የተፈጥሮ ደን ሀብትን ለመጠበቅ የደን አስተዳደር ፕላን ዝግጅት ተጀመረ
ጋምቤላ ፤ ጥር 6/2014(አዜአ)በጋምቤላ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ደን ሀብት ከሰደድ እሳትና ሌሎች ጥፋቶች ለመከላከል የአስተዳደር ፕላን ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ አካባቢ እና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የደን ተመራማሪ ዶክተር ምናሴ ጋሻው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ደቡባዊ ምዕራብ ሰፊ የተፈጥሮ የደን ሃብት ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል የጋምቤላ ክልል አንዱ ነው።
ይሁን እንጂ በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ደን ሀብት በአግባቡ ከመያዝና ከመጠበቅ አኳያ ችግሮች መኖራቸውን ይገልጻሉ።
በተለይም በሰደድ እሳት፣ ከግብርናና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በተፈጥሮ የደን ሀብቱ ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ምናሴ ገለፃ፤ ከሁለት አስርት ዓመት በፊት ባካሄዱት ጥናት ከደን ውድመት ጋር ተያይዞ በስፋት የነበሩ ነጭ ጆሮ ቆርኪ፣ ዝሆን፣ ጎሽና ሌሎች የዱር እንሳሳት እየተመናመኑ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ችግሩን ታሳቢ በማድረግ ኢንስቲትዮቱ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠበቅ የሰደድ እሳትንና ሌሎች ጉዳቶችን ለመቀነስ የተጠና የአስተዳደር ፕላን ለመስራት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ፕላኑን ለማዘጋጀት ከክልሉ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ጋር በመቀናጀት በአራት ወረዳዎች የተጀመረውን የቦታ መረጣና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ በሚቀጥለው ዓመት ይጠናቀቃል ነው ያሉት።
የክልሉ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ኡማን ኡጋላ ፤በክልሉ የተፈጥሮ ሀብት በደን ጭፍጨፋ፣ በሰደድ እሳት፣ በግብርና ኢንቨስትመንትና በሌሎች ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተፈጥሮ የደን ሀብቱ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ጥረት ሲደረግ ቢቆይም፤ደኑ ከሸፈነው የቆዳ ሽፋን አኳያ የተፈለገው ውጤት አልመጣም ብለዋል።
ኢንስቲትዮቱ የደን ሀብቱን ከጥፋት ለመታደግ የጀመረው የአስተዳደር ፕላን ዝግጅት እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ካለው 3 ሚሊዮን 420 ሺህ ሄክታር የቆዳ ስፋት 16 በመቶው በጥብቅ የተፈጥሮ የደን ሀብት መሸፈኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።