ለዓይን በሽታ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል- የኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
ለዓይን በሽታ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል- የኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ማህበር
አዲስ አበባ ነሀሴ 22/2010 የዓይን በሽታ እንደሌሎቹ በሽታዎች በመንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ማህበር አስታወቀ። ማህበሩ ከምስራቅ፣ መካከለኛውና ደቡብ አፍሪካ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ዓመታዊ ጉባዔውን ነገ በተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ "ለዓይን ህክምና ትኩረት መስጠት" በሚል መሪ ሀሳብ ያካሄዳል። የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዘላለም እሸቱ በሰጡት መግለጫ መንግሥት ለዓይን በሽታ ትኩረት ሰጥቶ በጤና ዕቅድ ውስጥ እንዲያካተት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የዓይን ህክምና ተቋማት እንዲከፈቱ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በአፋር፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የዓይን ህክምና እንደሌለ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ማህበር ከተመሠረተ 25 ዓመት ሲሆን በአሁኑ ወቅት 150 አባላት አሉት። ነገ በተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚጀመረው የማህበሩ ዓመታዊ ጉባዔ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።